
ከሚሴ፡ ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና በሚል መሪ መልእክት በአማራ ክልል የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም በመመለስ ከሕዝብ የሚነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል ሕዝባዊ ውይይት በከሚሴ ከተማ ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪዎች እንደተናገሩት ከግጭት እና ጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም። በመኾኑም ከግጭት በመራቅ ልማትን ማፋጠን ይገባል፤ መንግሥትም ሰላምን ለማስፈን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ከኅብረተሰቡ እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር እየተሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ሕዝቡም ለሰላም መስፈን እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንድሪስ አብዱ በአማራ ክልል የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ሽፋን በማድረግ የተፈጠረው ግጭት ክልሉን ስለመጉዳቱ ተናግረዋል።
አሁን ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኀይሎች በወሰዱት የሕግ ማስከበር ሥራ ክልሉ ወደ አንፃራዊ ሰላም ተመልሷል ነው ያሉት።
ሰላሙን ይበልጥ ለማጠናከር ሕዝቡ አሁንም የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።
የአፋር ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ኢሴ አደም ከግጭት እና ከጦርነት በመራቅ አንድነት እና ኅብረብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአንድነት የማይፈታ ችግር እንደለለም ነው የገለጹት።
ጥያቄ ያለው ማንኛውም ኀይል በዲሞክራሲያዊ መንገድ ማቅረብ አለበትም ብለዋል።
በጠመንጃ የሚፈታ ጥያቄ አለመኖሩንም ገልጸዋል።
ከሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እና የሕዝብ ደኅንነትን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል።
የሐረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ኦድሪን በድሪ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪዎች ለሰላም ዘብ በመቆማችሁ ሰላማችሁን መጠበቅ ችላችኋል ነው ያሉት።
በቀጣይም ከግጭት በመራቅ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብዝኃ ብሔር እና ሃይማኖት ሀገር መኾኗንም ነው ያስገነዘቡት።
መላው ሕዝብ የግጭት አስተሳሰብ እና ተግባርን መከላከል ይገባዋል ነው ያሉት።
ችግሮችን በመነጋገር በሀሳብ የበላይነት የመፍታት ባሕል ሊዳብር ይገባል ብለዋል።
መንግሥትም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ምንጊዜም ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል።
የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥም የሕግ ማስከበር ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
ከሕዝብ የሚነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በቀጣይ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰይድ አብዱ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!