
ባሕር ዳር: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጦፌ ሙሐመድ የአማራ ክልል ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉበት እንገነዘባለን ብለዋል። በአማራ ክልል ሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዳሉ ሁሉ ሌሎች ክልሎችም መሰል እና ሌሎች ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ ጥያቄዎች የሚፈቱትም ሰላም ሲረጋገጥ ነው ብለዋል።
አቶ ሙስጦፌ “ሰላም፣ ልማት እና ፍትሕ የኢትዮጵያ ሕዝብ የወል ጥያቄዎች ናቸው፤ እነዚህን የጋራ ጥያቄዎች በአንድነት በመቆም መፍታት እንጅ አንዱ የሌላውን ያለመገንዘብ አባዜ በሚፈጥረው ግጭት ሀገር እና ሕዝብን መጉዳት መቆም አለበት ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድር ሙስጦፌ በመነጋገር እና በመወያየት በአጭር ጊዜ ሊፈታ ለሚችል ጥያቄ 20 እና ከዚያ በላይ ዓመታትን ፈጅቶም ውጤት ወደማያመጣ የትጥቅ ትግል ማምራት ተገቢ አይደለም ብለዋል። “ችግሮችን ሁሉ በመሳሪያ ለመፍታት ማሰብ የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ጠንካራ የመወያየት ባሕል ሲኖር ብቻ ነው፤ ለዚህም እሴት አክባሪ ሕዝብ እና ጠንካራ አመራሮች ያስፈልጋሉ ብለዋል።
አንዱ በሌላው ጫማ ቆሞ ችግርን የማየት ልምድ የሚጎድለው የቆየ የፖለቲካ ባሕል ተቀይሮ በመተሳሰብ እና በጋራ ቆሞ ችግርን የመፍታት ባሕል መገንባት እንዳለበትም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የተፈጠረው ችግር የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ችግር ነው፤ በጋራ በመቆም የሕዝቡ ሰላም እንዲመለስም መሥራት ይገባል ነው ያሉት አቶ ሙስጦፌ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!