በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ድህነት እንዲወገድ እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ።

8

ገንዳ ውኃ: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና በሚል መሪ ሃሳብ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ምክክር ተካሂዷል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ሜካናይዝድ የኾኑ የእርሻ መሳሪያዎች እንዲቀርቡላቸው፣ የመስኖ ካናል፣ የዩኒቨርሲቲ መከፈት፣ የደረቅ ወደብ፣ የባቡር መንገድ፣ የአየር መንገድ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ በቂ የጤና ተቋማት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲገነቡ ጠይቀዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥም መንግሥት በትኩረት መሥራት አለበትም ብለዋል ተሳታፊዎቹ።

በአካባቢው የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ሕዝቡ ማውገዝ እና ወንጀለኞችን ለሕግ አሳልፎ በመስጠት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳደሪ ቢክስ ወርቄ ተናግረዋል።

ከእኔ በላይ ለሀገሬ የሚል እና በሀሳብ ልዕልና የሚያምን ትውልድ መገንባት ወቅቱ የሚጠይቀው ተቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።

ትውልዱ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን ከመቀበል መቆጠብ አለበትም ተብሏል።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ በኅብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ከትጥቅ ትግል ይልቅ በውይይት እንዲፈቱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

አሁን ላይ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።

የሽንፋ ወንዝን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ ትልልቅ ወንዞችን ለበጋ መስኖ አገልግሎት እንዲውሉ የመስኖ ሜጋ ፕሮጀክቶች መቀረጹንም ኀላፊው ተናግረዋል።

ዞኑ የበርካታ ጸጋዎች ባለቤት ቢኾንም ሙሉ አቅሙን አሟጦ ጸጋዎችን በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ የገለጹት ደግሞ የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አይናለም ንጉሴ ናቸው።

ግብርናውን ለማዘመን እና የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ መንግሥት የእርሻ መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከእር በርስ ግጭት እና ብጥብጥ ወጥቶ ለሰላም ዘብ መቆም ይገባልም ነው ያሉት።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አለሙ ስሜ (ዶ.ር) በመድረኩ ተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎች በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥቱ በጊዜ ሂደት የሚመለሱ ናቸው ብለዋል።

የዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት የሚያስችል ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱንም አንስተዋል::

በዞኑ የአውሮፕላን አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የባቡር መሥመር ዝርጋታ እና የደረቅ ወደብ ይከፈትልን ጥያቄዎች በጊዜ ሂደትና በየደረጃው ምላሽ እንዲያገኙ እንሠራለን ብለዋል።

መንግሥት አሁንም ቢኾን ለሰላም በሩ ክፍት ነው ያሉት ዶክተር አለሙ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የሰላም እና የልማቱ ባለቤት ሊኾኑ ይገባል ብለዋል።

በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ድህነት እንዲወገድ እና ብልጽግና እውን እንዲኾን እየተሠራ ነውም ብለዋል።

በአምስት ዓመት የለውጥ ጉዞ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በቴክኖሎጅ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ዶክተር አለሙ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምስጋና!
Next article“ጥያቄዎችን በመሳሪያ ለመፍታት ማሰብ የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ነው” ርእሰ መሥተዳደር ሙስጦፌ ሙሐመድ