“ከጥላቻና ግድያ የሚያተርፉ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንጂ እኛ ኢትዮጵያውያን ትርፍ የምናገኘው ከአብሮነትና አንድነታችን መጥበቅ ነው ” የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

11

ደሴ: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።

በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ ሕዝባዊ ውይይትም በደሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ ከ3ሺህ 600 በላይ ከደሴ ከተማና ከደቡብ ወሎ ዞን የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

በምክክር መድረኩ እያጋጠመ ያለው የሰላም እጦት እያስከተለ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግር በስፋት ተነስቷል፡፡ ከተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት በተጨማሪ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ አጥነትና የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተዳምረው ኅብረተሰቡን ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

በተለይ ለዓመታት እየተንከባለሉ የመጡ የአማራ ሕዝብ አንኳር ጥያቄዎች በተገቢው ጊዜና ፍጥነት ባለመመለሳቸው ዛሬ ላይ ለደረስንበት የሰላም እጦት ምክንያቶች መኾናቸውን የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት እና በታጠቁ ኃይሎች መካከል ከልብ የመነጨና ሀገርን ከትርምስ የሚያወጣ ውይይት ማድረግ ክልሉን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት የሁሉም ኅብረተሰብ ቀዳሚ ተግባር መኾን እንዳለበት ተነስቷል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና በሚኒስትር ማእረግ የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት አደረጃጃት ዘርፍ ኃላፊ ሳዳት ነሻ እያጋጠመ ያለው የሰላም እጦት መነሻ፤ በሀገራችን የረዥም ጊዜ ታሪክ የሥርዓት ለውጥ የሚመጣው በሀሳብ የበላይነት ሳይኾን አንዱ ሌላውን በማጥፋት ስለነበር ሂደቱ ዛሬም ድረስ ፈተና ኾኖብናል ብለዋል፡፡

አቶ ሳዳት አያይዘውም የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ ከሌሎች ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመኾን ነው ብለዋል፡፡

የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን በዘላቂነት መፍትሔ ለመሻት ብልፅግና ፓርቲ በፕሮግራም አካትቶ እየሠራ ለውጥም እያስመዘገበ መኾኑንም ነው ያነሱት አቶ ሳዳት፡፡ አንዱ ሌላውን በማጥፋት ቁርሾ እያስቀመጡ መሄድ ኢትዮጵያን ይጎዳልና ወደ ሀሳብ የበላይነት ማምራት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

በመድረኩ የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የሥራና ክህሎት ሚንስትር ሙፈሪሃት ካሚል “ከጥላቻና ግድያ የሚያተርፉ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንጂ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ትርፍ የምናገኘው ከአብሮነትና አንድነታችን መጥበቅ ነው ” ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብን ጥያቄ እናስመልሳለን በሚል ሽፋን አማራ ያለውን እንዲያጣ ማድረግ አይገባም ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል የአማራ ሕዝብ ህመም የኢትዮጵያውያን ሁሉ ህመም ነው ነው ብለዋል፡፡

በመኾኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ችግሮችን በሰላማዊ አማራጭ ብቻ እንዲፈቱ መሥራት ይገባል፤ መንግሥትም ለሰላማዊ ውይይት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

ያሉብንን ፖለቲካዊ ስብራቶች በሠለጠነ እና መደማመጥን መሰረት ባደረገ መልኩ መፍታት እንጂ በጠመንጃ ለማስመለስ መጓዝ አያስፈልግም ሀገራችንንም ይጎዳል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ፊኒክስ ሀየሎም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከአንድ ወገን ብቻ የኾነ ሆደ ሰፊነት እና ሰላም ወዳድነት ዘላቂ ሰላምን አያመጣም፤ በመኾኑም ሁሉም ለሰላም ሊተባበር ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleስለሰላም ፍቱን ሃሳቦችን ማንሳት፣ መወያየት እና የድርሻን መውሰድ አስፈላጊ እንደኾነ ተገለጸ።