“ከአንድ ወገን ብቻ የኾነ ሆደ ሰፊነት እና ሰላም ወዳድነት ዘላቂ ሰላምን አያመጣም፤ በመኾኑም ሁሉም ለሰላም ሊተባበር ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

19

ባሕር ዳር: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።

“ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ መልእክት በባሕር ዳር ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋየ በልጂጌ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጦፌ ሙሁመድ እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ውይይቱን መርተዋል።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ውይይቱ በሀገራዊ አንድነት እና ብሔራዊ መግባባት ላይ የተመሠረተ ሰላም እንዲሰፍን ያግዛል ብለዋል። በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ ከፍተኛ የኾነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት አስከትሎ ማለፉንም ጠቁመዋል። አሁን ላይ የክልሉ ሰላም በአንጻራዊነት እየተሻሻለ መምጣቱን እና ሊደርስ ከነበረው ቀውስ ሕዝብን መታደግ መቻሉን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች እንዳሉት ይታወቃል፤ ይህንንም የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት በውል ይገነዘቡታል፤ ምላሽ ለመስጠትም እየተሠራ ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።

የሕዝብን ፍትሐዊ ጥያቄዎች ከለላ አድርጎ ክልሉን ወዳልተገባ ብጥብጥ ለማስገባት መሞከር ግን ለሕዝብ ካለማሰብ የሚመነጭ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ጥያቄ እና ጥቅም ከኢትዮጵያ አንድነት ጋር ተጣጥሞ እንዲመለስ ነው የምንፈልገው፤ ለዚህም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመኾን ለመፍታት እንሠራለን ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።

“የሰው ልጅ ጥያቄ አያበቃምና ጥያቄ በመጣ ቁጥር ጦርነት አንስተን እንዘልቃለን ወይ?” ሲሉ ያጠየቁት ርእሰ መሥተዳድሩ ጥያቄ እና ፍላጎትን በትዕግስት እና በስክነት ማቅረብ፣ መወያየት እና ለመፍትሔው በጋራ መሥራት ሊለመድ ይገባል ብለዋል።

የቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላም የተመለሱ በርካታ ወገኖች እንዳሉ እና አሁንም ድረስ በሕገ ወጥ ድርጊት ላይ የቀጠሉ ሰላምን የማይፈልጉ እንዳሉም አንስተዋል። መንግሥት ለሰላም ቁርጠኛ ነው፣ ነገሮችን በሆደ ሰፊነት እያየም የሰላም አማራጮችን በየጊዜው እያቀረበ ነው ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ “ከአንድ ወገን ብቻ የኾነ ሆደ ሰፊነት እና ሰላም ወዳድነት ዘላቂ ሰላምን አያመጣም” ሲሉም ገልጸዋል። ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ማንኛውም ጥያቄ በውይይት እንዲፈታ፣ የክልሉ ሕዝብም ሠርቶ ከድህነት እንዲወጣ ሁሉም ወገን የሰላም ፍላጎትን ሊያሳይ ይገባል ነው ያሉት። የሰላም በሩን ዘግቶ ሕገ ወጥ ድርጊት እየፈጸመ ሕዝብን የሚያንገላታ አካል ሲገጥም ግን ሕግን በመደበኛነት ማስከበር የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር መኾኑ አይቀሬ ነው ብለዋል።

ለሀገር የወደቀ እና ሀገር ያጸናውን የአማራ ሕዝብ ሀገር ወደሚያጠፋ አውዳሚ ጦርነት ለመክተት መሞከር ስህተት ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።

የኑሮ ውድነት መባባስ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የአማራ ክልል ሕዝብንም እየፈተነ መኾኑን እንረዳለን፤ ክልሉ ሰላም በማጣቱ ግን ችግሩን ለመቅረፍ የሚሰራው ሥራ አስፈላጊውን ለውጥ እንዳያመጣ አድርጎታል ብለዋል።

የክልሉ ሰላም ሲሰፍን ተጨባጭ የኑሮ ውድነት ቅነሳ ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚመችም አመላክተዋል። የኑሮ ውድነትን ትርጉም ባለው መልኩ ለማሻሻል በመንግሥት በኩል የተለያዩ ጅምር ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። ሥራዎችን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ግን ሕዝቡ የየአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በክልሉ ተከሰተው የድርቅ አደጋ የፈጠረው ጉዳት ስለመኖሩ የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እርዳታ ለማድረስም ቅድሚያ ሰላምን ማስፈን ግድ እንደሚል አስገንዝበዋል።

የክልሉ ሕዝብ በርካታ የልማት ጥያቄዎች አሉት፤ ጥያቄዎችን በቅደም ተከተል ለመፍታት የሁሉም ነገር መሠረት የኾነውን ሰላም ማስፈን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ርእሰ መሥተዳድሩ ዛሬ በተደረገው ውይይት ወደ ክልሉ በመምጣት የሕዝቡን ጥያቄዎች ላዳመጡት የፌዴራል እና ለሌሎች ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ምስጋና አቅርበዋል። እንዲህ አይነት ውይይቶችን ማካሄድ የአንዱ ችግር ለሌላችንም ችግር መኾኑን እና ለመፍትሔውም በጋራ የምንቆም መኾናችንን ማሳያ ነው ብለዋል። ሕዝብ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለቅሞ በመያዝ በጋራ ለመፍታት እድል የሚሰጥ ስለመኾኑም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም እጦት የሚያስከትለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት በመገንዘብ ኅብረተሰቡ ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።
Next article“ከጥላቻና ግድያ የሚያተርፉ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንጂ እኛ ኢትዮጵያውያን ትርፍ የምናገኘው ከአብሮነትና አንድነታችን መጥበቅ ነው ” የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል