የሰላም እጦት የሚያስከትለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት በመገንዘብ ኅብረተሰቡ ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

25

ሀሁመራ: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።

“ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን ለዘላቂ ሰላም እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ መልእክት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝባዊ የሰላም ውይይት ተካሂዷል።

ሰላም የሁሉም ዋስትና መኾኑን ለማረጋገጥ በተካሄደው የውይይት መድረክ የዞን አመራሮች ፤ የሃይማኖት አባቶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከጦርነት ይልቅ ሰላምን አማራጭ ማድረግ እንደሚገባ አንስተው የሰላም እጦት የሚያስከትለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት በመገንዘብ ኅብረተሰቡ ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት የወሰንና የማንነት ጥያቄ ያለው በመኾኑ መንግሥት ማንነታችንን በሕግ አግባብ እውቅና ሊሰጠን ይገባል በማለት ጠይቀዋል።

በዞኑ በጀት ባለመኖሩ በጤና፣ በትምህርት እና በተለያዩ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረግ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዳንኾን አድርጎናል ያሉት ነዋሪዎቹ መንግሥት ለዞኑ ሕዝብ በጀት እንዲመድብም ጠይቀዋል።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ እና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አሸተ ደምለው ሀገራዊ የለውጥ ንቅናቄ እውን ከኾነበት ጊዜ ጀምሮ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ያለማንም ከልካይነት በነጻነት በአደባባይ የማንነት ጥያቄውን ማቅረብ እንዲችል ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሯል ነው ያሉት።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ጥያቄ በሕገ አግባብ ምላሽ እስኪያገኝ አንድነቱን አስጠብቆ ይዘልቃል ያሉት አቶ አሸተ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ባሻገር ለሀገር አንድነት ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል።

ወንድም ወንድሙን በመግደል ጦርነትን አማራጭ በማድረግ የሚፈታ ጥያቄ ባለመኖሩ የሰላም ውይይት እና ንግግር በማድረግ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ የእውነትና የፍትሕ ጥያቄ በመኾኑ የዞኑ አሥተዳደር የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

ዞኑ ያለ በጀት የሚንቀሳቀስ ቢኾንም በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አንስተዋል።

የዞኑ ሕዝብ የበጀት ተጠቃሚ እንዲኾን በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ለውይይቱ ተሳታፊዎች አረጋግጠዋል።

በዞኑ የፍትሕ ተቋማት አገልግሎትን በቅርብ ጊዜ ለማስጀመር እየተሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረ እግዚአብሔር ደሴ የሀገሪቱን ውስጣዊ ሰላም ለማረጋገጥ አንድነትን በማስቀደም ኅብረ ብሔራዊነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት እና ድጋፍ በማድረግ ሰላምን አስጠብቆ ሊዘልቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ – ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላም የኾኑ አካባቢዎች ሰላማቸውን አስጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ተቀራርቦ መወያየት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
Next article“ከአንድ ወገን ብቻ የኾነ ሆደ ሰፊነት እና ሰላም ወዳድነት ዘላቂ ሰላምን አያመጣም፤ በመኾኑም ሁሉም ለሰላም ሊተባበር ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ