ሰላም የኾኑ አካባቢዎች ሰላማቸውን አስጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ተቀራርቦ መወያየት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

19

ደባርቅ: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።

በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ አሥተዳደር “ፈተናዎችን ተሻግረን የኢትዮጵያን ልዕልና በጋራ እንሠራለን፤ በአንድነት ስንቆም ህልውናችንን እና ክብራችንን እናስጠብቃለን” በሚል መሪ መልእክት ውይይት እየደረገ ነው። በሰላም፣ ልማት እና መልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ ከኹሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ነው ሕዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ የሚገኘው።

በመድረኩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል ጸጋዬ ማሞ፤ የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አብርሃም ማርሻሎ፤ የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ፤ የሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የውይይት መድረኩ መሪ የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል አብርሃም ማርሻሎ የውይይቱ ዓላማ በየአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለማዳመጥ፤ የሚነሱ ችግሮች በሚፈቱባቸው መንገዶች ላይ ለመስማማት፤ የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ በተለይም ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ለማድረግ፤ ሰላም የኾኑትን ደግሞ ሰላማቸውን ለማስቀጠል የተፈጠረ መድረክ መኾኑን ተናግረዋል።

ሥራ አስፈጻሚው አብረሃም ማርሻሎ ማኅበረሰቡ በሰላም እጦት በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በሌሎች ጉዳዮች ተጽእኖ እንደደረሰበት ተናግረዋል። በሰላም እጦት ችግሩ ክልሉ ብሎም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መጎዳቱን ተናግረዋል። አሁን ላይ የክልሉ ሕዝብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና የጸጥታ ኀይሉ በጥምረት ለሰላም በመሥራታቸው የአማራ ክልል የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን አንስተዋል።

ይሁን እና ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ፤ ሰላም የኾኑ አካባቢዎች ሰላማቸውን አስጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ በሰላማዊ መንገድ ተቀራርቦ መወያየት፤ ችግርን እና የሚፈቱበትን አግባብ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ክልሉ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ እንዲተዳደር ሰላም መስፈን አለበት። ለዚህም ማኀበረሰቡ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት አለበት ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም ለሰላም እጦት መነሻ ናቸው፤ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን አካባቢያዊ፣ ዞናዊ፣ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ዘጋቢ :- አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አስተዋዩ የአማራ ሕዝብ ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ቀድሞ የመገኘት ታሪክ ነው ያለው” ተስፋየ በልጂጌ
Next articleየሰላም እጦት የሚያስከትለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት በመገንዘብ ኅብረተሰቡ ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።