“አስተዋዩ የአማራ ሕዝብ ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ቀድሞ የመገኘት ታሪክ ነው ያለው” ተስፋየ በልጂጌ

19

ባሕር ዳር: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።

“ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ መልእክት በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደውን ሕዝባዊ ውይይት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋየ በልጂጌ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጦፌ ሙሁመድ እና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው መርተውታል።

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋየ በልጂጌ በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕዝቡን እና ክልሉን ከከፋ ችግር ታድጓል፤ ለዚህም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሕዝብ ጎን ቆሞ ለከፈለው መስዕዋትነት ክብር እና ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

መከላከያ ሠራዊት በሕዝቡ ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይ ከፍቸኛ የኾነ የጥላቻ ዘመቻ ቢከፈትበትም ሕዝቡ የሃሰተኞችን ወሬ ወደ ኃላ በመተው እና ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ለሰላም ሲሠራ መቆየቱ የአርቆ አሳቢነት ምልክት ነው ሲሉም አብራርተዋል።

ሚኒስትሩ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ተጨማሪ ማብራሪያም ሰጥተዋል። ከክልሉ ውጭ ከሚኖሩ አማራዎች ደኅንነት ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ጥያቄ መንግሥት በሚገባ እንደሚገነዘብ አቶ ተስፋየ ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ በሰላም እንዲኖር ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ከወሰን እና ማንነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችም ሕግ እና ሥርዓትን ባማከለ እና ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ በዘላቂነት እንዲፈቱ መንግሥት በትኩረት ይዞ እየሠራበት ነው፤ በተግባርም የተከናወኑ ሥራዎች አሉ ብለዋል።

አቶ ተስፉየ ከሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ “የአማራን ሕዝብ ፍላጎት የማይገነዘብ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሊኾን አይችልም” ሲሉም መልሰዋል። ሁሉምንም ኢትዮጵያዊያን በሚወክል እና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ለማሻሻል በመንግሥት በኩል እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

አንድ ከሚያደርጉ ይልቅ የቆየ ሕብረ ብሔራዊ ወንድማችነት እና እሕትማማችነታችንን የሚንዱ ትርክቶች መገንባታቸው ሀገር እና ሕዝብን ዋጋ እያስከፈሉ እንደኾነም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የአማራ ክልል ሕዝብም በተዛቡ ትርክቶች ሰበብ ከባድ ዋጋ እየከፈለ ስለመኾኑ መንግሥትም በውል ተረድቶታል ነው ያሉት። ይህ እንዲፈታ ሁላችንንም የሚጠቅም፣ በአንድነት ላይ የተመሠረተ፤ እንደ ሀገር ያቆመንን ትክክለኛ የጋራ ታሪካችንን የቃኘ እና በአንድነት የሚያኖረንን ትርክት አጥብቆ መያዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አቶ ተስፋየ በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም ችግር እንዴት መፈታት እንዳለበት ለተነሳው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ “ከአፈ ሙዝ የሚገኝ አንዳች ሰላም የለም” ብለዋል። መንግሥት ለሰላም ቁርጠኛ ነው፣ የጦርነት አሸናፊ እንደሌለውም ያውቃል ነው ያሉት።

ይሁን እንጅ መንግሥት የሚያቀርበውን የሰላም ጥሪ እንደድክመት እና ተሸናፊነት የሚቆጥሩ አካላት ሕዝብን ለከፋ ጦርነት ሲቀሰቅሱ ተስተውሏል ብለዋል። መንግሥት ግጭት እንዳይቆም የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውን በተረዳ ጊዜ ከሕዝብ ጋር በመኾን ሕግን ማስከበሩ የማይቀር ነገር ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

በመኾኑም ለሀገር እና ለሕዝብ የሚያስብ ሁሉ መሳሪያውን አስቀምጦ የሃሳብ ንግግር ማድረግ አለበት፤ ያኔ የመደማመጥ ጊዜ ይመጣል፤ ጥያቄዎችም ይፈታሉ፤ ሰላምም ይሰፍናል ብለዋል።

ሰላም ወዳድ የኾነው የአማራ ሕዝብ እና አመራሮቹ በክልሉ የተፈጠረው ችግር ተቀርፎ አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉም አቶ ተስፋየ ተናግረዋል። “አስተዋዩ የአማራ ሕዝብ ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ቀድሞ የመገኘት ታሪክ ነው ያለው” ሲሉ ገልጸዋል። አስተዋዩ ሕዝብ አሁንም ቢኾን ነገሮችን ሰክኖ በማየት ክልሉ ሰላም እንዲኾን መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላም እና በሕግ አግባብ የሚፈቱባት ሰላም የተረጋገጠባት ሀገር የማድረግ ሥራ መሥራት ይገባናል” የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ
Next articleሰላም የኾኑ አካባቢዎች ሰላማቸውን አስጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ተቀራርቦ መወያየት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።