“የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላም እና በሕግ አግባብ የሚፈቱባት ሰላም የተረጋገጠባት ሀገር የማድረግ ሥራ መሥራት ይገባናል” የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

10

ደብረ ታቦር፡ ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።

“ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ መልእክት በደብረ ታቦር ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ርስቱ ይርዳው እና የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን ከተማዋ ለኑሮ ተስማሚ ነዋሪዎቿ እንግዳ ተቀባይ እና ጥንታዊት ናት ብለዋል። ደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ የተቋቋመባት እና በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መናገሻ የነበረች መኾኑንም አንስተዋል።

ከተማዋ ከእድሜዋ ጋር የሚጣጣም የእድገት ደረጃ ላይ አለመኾኗንም ገልጸዋል ። ከተማዋን ለማልማት የተጀመሩ ሥራዎች በጸጥታ ችግር ተስተጓጉለው መቆየታቸውን አስታውሰዋል ። የጸጥታ ሁኔታው የከተማዋን እድገት ለማፋጠን ፈታኝ እንደኾነም አንስተዋል።

በጸጥታ ሥራ መጠመድ መደበኛ ሥራ እንዳይሠሩ፣ ለወጣቶች የሥራ እድል እንዳይፈጠር እና ነጋዴዎች እንዳይነግዱ ማድረጉንም ገልጸዋል። የሰሜኑ ጦርነት ያደረሰው ዳፋ ሳይቀረፍ አሁን የተፈጠረው ችግር ከተማዋን መጉዳቱንም አንስተዋል። ችግሮችን ለመፍታት እና የጸጥታ ሁኔታውን ለመመለስ በጥልቀት መምከር እና መፍትሔ ማስቀመጥ ይገባናል ብለዋል። ወጣቶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ለሰላማቸው ዘብ መቆም እንደሚገባም ገልጸዋል።

የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም በጥልቀት በመምከር ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ይገባናልም ብለዋል። ሰላምን መሠረት አድርገን ከተወያየን ዘላቂ ሰላምን አምጥተን ወደ ልማት መግባት እንችላለን ነው ያሉት። የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግንባታ እንዲፋጠን፣ በጋፋት ላይ ሊሠራ መሠረተ ድንጋይ የተቀመጠበት የብረታብረት ኢንዱስትሪ እንዲሠራ ጠይቀዋል። ከንቲባው ሕዝብ የሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱም ጥያቄ አቅርበዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ በኅብረብሔራዊነት ስሜት የኢትዮጵያን ልዕልና ከፍ ማድረግ ይገባናል ብለዋል።

ከችግር ጎን ለጎን ለሀገር አንድነት እና ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ በትክክለኛው መንገድ እየሄድን መኾናችን የሚያሳዩ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል። ሀገር የትብብር ሥራ ውጤት መኾኗንም ገልጸዋል። ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መኾኑን በመረዳት ለሰላም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አንስተዋል። የተዛባውን አመለካከት በማስቀረት ትክክለኛውን ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። በዞኑ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ከሚኾኑ ወገኖች ጋር ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል።

የተሟላ ሰላምን ለመገንባት የሚያስችል ቁመና ላይ እንገኛለንም ብለዋል። የልማት ሥራዎችም እየተካሄዱ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ከሕዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

በዞኑ እየተገነቡ ያሉ የርብ መስኖ ፕሮጄክት ፣ የወረታ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ፣ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ገብርዬ ካምፓስ፣ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲፈቱላቸውም ጠይቀዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ግጭት በቃኝ ልማት እንፈልጋለን እያለ መኾኑንም ገልጸዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የብልጽግና ፓርቲ ባደረገው የሥራ አስፈፃሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ ሰብሰባ ዘላቂ ሰላምን እንዲመጣ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

እህትማማችነት እና ወንድማማችነት እንዲጠናከር አቅጣጫ መቀመጡንም አመላክተዋል። የኢትዮጵያን ዘላቂ የልማይ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሌላው አቅጣጫ የተቀመጠበት ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል። ሰላምን ማረጋገጥ እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በትኩረት ይሠራል ብለዋል። ይህን ለማድረግ መሪዎች ከሕዝብ ጋር እንዲወያዩ መፈለጉንም ተናግረዋል።

የውይይቱ ዋና ዓላማ ሕዝብን ቀረብ ብሎ ለማዳመጥ መኾኑንም ገልጸዋል። ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በሠራው ሥራ አንፃራዊ ሰላም እየሰፈነ ቢኾንም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከሕዝብ ጋር ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መወያየት ይገባልም ብለዋል። በክልሉ አሁንም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሥራዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።

የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላም እና በሕግ አግባብ የሚፈቱባት ሰላም የተረጋገጠባት ሀገር የማድረግ ሥራ መሥራት ይገባል ብለዋል። በጸጥታ ችግሮች እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መምጣታቸውንም ተናግረዋል። በጋራ መክረን ክልሉ ወደ ተሟላ ሰላም እንዲደርስ መግባባት እና በጋራ መሥራት ይገባናል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልሉ የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም አስተማማኝ በማድረግ፣ የክልሉን ሁለንተናዊ ልማት ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳድር እንጅባራ ከተማ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያለመ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
Next article“አስተዋዩ የአማራ ሕዝብ ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ቀድሞ የመገኘት ታሪክ ነው ያለው” ተስፋየ በልጂጌ