
ኢንጅባራ: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳድር እንጅባራ ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ ውይይትም በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ እና ሌሎችም የክልልና የፌዴራል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ከብሔረሰብ አሥተዳድሩ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶችም በውይይቱ ተሳትፈዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳድር አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው መድረኩ በክልሉ ባለው ሁለንተናዊ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አሥተዳድር ጉዳዮች ላይ ለመምከር የተዘጋጀ ነው ብለዋል። ሰላም የሁሉም ነገር ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ የገለፁት ዋና አሥተዳዳሪው የብሔረሰብ አሥተዳድሩ ሕዝብም ለሰላም የሚተጋ ነው ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ውይይቱ በክልሉ የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ፣ የክልሉን ሁለንተናዊ ልማትና ሀገራዊ አንድነትን ለማስቀጠል ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት፣ ከሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ባለፈ በዜጎች ላይ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ፈጥሮ አልፏል። ካለፈው ጥፋት በመማርም በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማስተካከልና ለሰላም መረጋገጥ ሁሉም ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
የሕዝብን የልማትና የመልካም አሥተዳድር ጥያቄዎች ለመፍታት ሰላም ያስፈልጋል ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ በተሠራው ሥራም አንፃራዊ ሰላም መገኘቱን አንስተዋል።
የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ በክልሉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል የፍትሕና የፖሊስ ተቋማትን የማደራጀትና የማጠናከሩ ሥራም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳድር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ አንድ ባለመኾናችን ሀገሪቱ የገጠማትን የፖለቲካ ስብራት መጠገን አልተቻለም፤ ለዚህም መፍትሔው እንደ ሀገር በጋራ መቆም አለብን ብለዋል። በመረዳዳትና በአብሮነት የሕዝብ ጥያቄዎች እንደሚችሉ በሰከነ መንገድ መገንዘብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የልማትና የመልካም አሥተዳድር ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳድሩ በተለይም ከመሬት አሥተዳድር ጋር በተገናኘ ብልሹ አሠራር እንዳለ፣ የመሠረተ ልማት ችግር፣ የመማሪያ መጽሐፍት እጥረ መፍትሔ ሊሠጠው እንደሚገባ ተናግረዋል። መንግሥት የሚነሱ የሕዝብን ጥያቄዎች በፍትሐዊነትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊፈታ ይገባል ብለዋል። ሁሉም ለሰላም የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ለሰላማችን ቅድሚያ ሰጥተን መሥራት ከቻልን የልማትና የመልካም አሥተዳድር ጥያቄዎቻችን ይፈታሉ ብለዋል።
በቂ የመማሪያ መጽሐፍት ታትሞ በፀጥታ ምክንያት በክዘና ማዕከል እንደሚገኝና ጥያቄዎችን እንደ ግብዓት በመውሰድ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!