
ሰቆጣ: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 15 ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል።
የውይይት መድረኮችን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥት እና የሌሎች ክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች መርተዋቸዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማም ሕዝባዊ አንድነት እና ሰላምን ለመፍጠር ያለመ ውይይት ተካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጎን ነን፤ የፌዴራሉ መንግሥት እና የክልሉ መንግሥት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ሊመልሱ ይገባል ብለዋል።
ወይዘሮ እቴኑ አድማስ የዋግ ኽምራ ሕዝብ ከልማት ጋር ያልተገናኘ ሕዝብ ነው፤ ይህንንም ተደጋግሞ ተነስቷል መንግሥትም ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
ሊቀ ኅሩያን ኃይሌ አለሙ የሰሃላ ድልድይን ለመሥራት የክልሉ መንግሥት ስለጀመረልን እናመሠግናለን፤ የአስፓልት እና የጤና ተቋማትንም እንድትገነቡልን ብለዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የክልሉ መንግሥት የዋግን ችግር ለመቅረፍ በቁርጠኝነት እየሠራ እንደኾነ ገልጸዋል።
በዋግ አካባቢ ይንቀሳቀስ የነበረውን ኀይል ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመጣ ላደረጋችሁት ሥራ ከፍ ያለ ምሥጋና ይገባችኋልም ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ብልጽግና ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እስከታችኛው ደረጃ ወርዶ እየሠራ ነው እናንተም ከጎኑ ልትቆሙ ይገባል ብለዋል።
የኦሮሚያ ሕዝብ እና መንግሥት ወንድምነቱን ለማሳየት በሰቆጣ ከተማ የጀመረውን የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ በቅርብ ቀን አጠናቅቆ ያስረክባችኋልም ብለዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ.ር) የዋግ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በቀጣይ ልታስቀጥሉት ይገባል ብለዋል።
መንግሥት ሰላም ብቸኛ የእድገት መግቢያ በር ነው ብሎ ያምናልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት እየጠበቀ ሀገርን ከመፍረስ የታደጋትን መከላከያን መደገፍ ይገባል ያሉት ዶክተር አብርሃም ከሰላም ልማት፣ እድገት እና ብልጽግና ይገኛል ብለዋል።
የቀረቡ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በክልሉ አቅም የሚፈቱ ጥያቄዎችን በክልሉ፤ በፌዴራሉ መንግሥት የሚፈታውን በፌዴራል መንግሥት ለመፍታት እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!