በጎንደር ከተማ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ግንባታ እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር እና የሲዳማ ክልል ገለጹ።

14

ባሕር ዳር: ጥር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ እና የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሊዳሞ በጎንደር ከተማ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በጎንደር ከተማ ለምገባ ማዕከሉ የሚውሉ ሁለት ቦታዎች ላይ ጥናት የተደረገ ሲኾን አንዱ የምገባ ማዕከል የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሀይ ገልጸዋል።

በጎንደር ከተማ ተገኝተው ለጎንደር የሚያስፈልጋትን የምገባ ማዕከል የመሠረት ድንጋይ ላስቀመጡት ከንቲባ አዳነች አበቤ እና ለርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሊዳሞ ምሥጋና ያቀረቡት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጎንደር ከአዲስ አበባ ከተማ ልምድ በመውሰድ እንደምትሠራ ገልጸዋል።

የምገባ ማዕከሉ በጎንደር በዝቀተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

የምገባ ማዕከሉ ግንባታ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ መኾኑን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ ገልጸዋል። የምገባ ማዕከሉን አዲስ አበባ ከተማ ሙሉ ወጪውን በመሸፈን እንደሚገነባም ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ብልጽግና ሰው ተኮር በመኾኑ ሥራዎች እንዲሳኩ ይደረጋል ብለዋል። አዲስ አበባ እና ጎንደር ከተማ እህትማማች ከተሞች ናቸው ያሉት ከንቲባዋ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ተሞክሮ እንደሚያጋሩም ገልጸዋል።

“በመተባበር ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ላይ እንሠራለን ያሉት ከንቲባዋ የተስፋ ምገባ ማዕከሉ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችን ይቀጥላል” ብለዋል።

 

የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሊዳሞ በተስፋ የምገባ ማዕከሉ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ በመገኘቴ ደስታ ይሰማኛል፤ የሲዳማ ሕዝብ አካፍሎ የሚበላ ነውና የምገባ ማዕከሉ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸው እንደማይለየው አስረድተዋል።

ያለን አካፍሎ መብላት ልማዱ የኾነው የሲዳማ ሕዝብም ለዚህ ማዕከል የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በዚህ ፕሮግራም የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለ ማርያም ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተል ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።
Next article“የዋግ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በቀጣይም ልታስቀጥሉት ይገባል” የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ.ር)