የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተል ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።

25

ባሕር ዳር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የሴቶችን የልማት ኅብረት ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል። የውይይቱ ዓላማ የሴቶች አደረጃጀቶችን በማጠናከር በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሃብት እና በማኅበራዊ ዘርፍ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ መኾኑ ተጠቅሷል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ጉዳይ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ቀጣይነት ያለው ልማት፣ ሰላም እና መልካም አሥተዳደርን በማስፈን እና ድህነትን ለማስወገድ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ሴቶችም የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል በመኾናቸው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ምቹ ፖሊሲ፣ የሕግ ማዕቀፍ፣ ስትራቴጂ እና አሠራር ተቀርጾ እየተሠራም ነው ብለዋል። ይህ መድረክም ለሴቶች ተጠቃሚነት የተሰጠው ትኩረት ማሳያ መኾኑን ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ሴቶችን ያላሳተፈ የልማት ሥራ በውጤቱም የሚጠበቀውን ያህል ሙሉ እንደማይኾን ገልጸው ሴቶች ለቤተሰብ እና ለሀገር እድገት ያላቸውን መሰረት ጠቅሰዋል። የልማት እንቅስቃሴም ውጤታማ የሚኾነው ሴቶች እኩል ሲሳተፉ እና ተጠቃሚ ሲኾኑ ነው ብለዋል። በአማራ ክልልም የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሠራ ሥራ ሴቶች ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል። ይህ የልማት ኅብረትም ሴቶች በየአካባቢያቸው ተደራጅተው በመወያየት እና በመሥራት ተጠቃሚ የሚኾኑበት አደረጃጀት ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሴቶች ሕጻናት እና ወጣቶች ክፍል አስተባባሪ ዶክተር ትዕግስት ብሩ የሴቶች የልማት አደረጃጀት ለጤና ቢሮ ሥራዎች ምቹ እና ለጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ውጤታማነት አጋዥ መኾኑን ገልጸዋል። እናቶች የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉ፣ በጤና ተቋም እንዲወልዱ እና ቤተሰብ መጸዳጃ ቤት እንዲኖረው በማድረግም ያግዛል ብለዋል። ጤና ቢሮውም አደረጃጀቱን ለማጠናከር የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ አደረጃጀቶች የሥራ ማሳለጫ እንጅ ግቦች ባለመኾናቸው አጋር አካላት እንደየተቋማቸው ምቹ ሁኔታ እንዲተገብሩ አሳስበዋል። ምክር ቤታቸውም የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በትኩረት በመከታተል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በውይይቱ የልማት ኅብረቱ ማቋቋሚያ ረቂቅ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። የአደረጃጀት፣ የአሠራር፣ የሥራ ግንኙነት፣ የሚጠበቁ ውጤቶች እና ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶች ላይ ውይይት ተደርጎ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አጅባር በሰው ተመላች፤ ከዳር ዳር ተጠበበች”
Next articleበጎንደር ከተማ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ግንባታ እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር እና የሲዳማ ክልል ገለጹ።