“አጅባር በሰው ተመላች፤ ከዳር ዳር ተጠበበች”

41

ደብረ ታቦር: ጥር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ታቦታቱ የሚያድሩባት፣ ሊቃውንቱ የሚልቁባት፣ ባማሩ ፈረሶች የተዋቡት የሚገማሸሩባት አጅባር ከዳር ዳር በሰው ተመላች፤ ተጠበበች።

ምዕምናኑ አስጨነቋት፣ ፈረሰኞቹ ከበቧት። ሊቃውንቱ የከበረውን ሥርዓት ፈፀሙባት። በአጅባር የታየውን የከበረ ሥርዓት እና የጸና ሃይማኖት ማን ችሎ ይገልጸዋል? ማንስ ችሎ ይናገረዋል? እፁብ ብሎ ያለፈዋል እንጂ።

በቀደመው ዘመን ነገሥታቱ በክብራቸው የተቀመጡባት፣ ስለ ሀገር አንድነት፣ ስለ ሀገር ፍቅር እና ስለ ነፃነት የመከሩባት፣ ጠጅ እያዘነበሉ፣ ጮማ እየቆረጡ ግብር ያበሉባት፣ ልዑላኑ፣ መሳፍንቱ የፈረስ ጉግስ የተጫወቱባት፣ ታሪክ ያስቀመጡባት፣ ሠንደቅ ያስከበሩባት አጅባር በበዓለ መርቆሬዎስ ደምቃ ዋለች።

መለኮት በተገለጠበት የታቦር ተራራ ስሟን የወሰደችው፣ በየኮረብታዎቿ አድባራትን የደበረችው፣ በሊቃውንት እና በጀግኖች የተመላችው ደብረ ታቦር ጎዳናዎቿ በሰው ተጨነቁ፣ ስለ ታቦተ ክብር ዝማሬው ከዳር ዳር ተሰማ፣ እልልታው በረታ፣ ሆታው ከፋለ፣ ፈረሰኞቹ ለታቦቱ ክብር የሚገባውን አደረጉ።

በደብረ ታቦር በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ በዓል አንደኛው ነው። በቆየው የአባቶች ባሕል እሴት በፈረስ ጉግስ የሚታጀበው በዓለ መርቆሬዎስ ለምዕምናንም ኾነ ለጎብኝዎች በጉጉት ይጠበቃል።

በዚያ ታላቅ በዓል ለመገኘት የሚመኙ እና የሚጓጉ ሁሉ ለአምላከቸው ስለት እየተሳሉ ለዓመት እንዲያደርሳቸው አደራ እየሰጡ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። ስለታቸው ደርሶ ዓመት በመጣ ጊዜ ስለታቸውን እየያዙ እልል እያሉ ይመጣሉ። የአምላክ ክብር የሚገለጥበትን ታቦቱን አጅበው ይገኛሉ። በአጅባርም ሲያመሰግኑ አድረው ሲያመሰግኑ ይውላሉ።

ፈረሰኞችም ለዓመት ይሳላሉ። ዓመት ከደረሱ ሠጋር ፈረሳቸውን፣ አስውበው ታቦቱን ሊያጅቡ ሥለት ያገባሉ። ስለታቸው በደረሰች ጊዜ ፈረሶቻቸውን አስውበው፣ አምረው ወደ አጅባር ይመጣሉ። በአጅባርም ታቦቱን እያጀቡ ይውላሉ። አጅባር ታሪክን የሚነገርበት፣ ሃይማኖት የሚሰበክበት፣ ስለ አንድነት የሚመከርበት፣ ስለ ፍቅር የሚዘከርበት ታላቅ ምድር።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዓለ መርቆሬዎስ የእቴጌ ጣይቱ ሐውልት ከተመረቀበት ቀን ጋር ተያይዞ መከበሩ ድምቀቱን ድርብ ያደርገዋል” አቶ ጥላሁን ደጀኔ
Next articleየአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተል ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።