“በዓለ መርቆሬዎስ የእቴጌ ጣይቱ ሐውልት ከተመረቀበት ቀን ጋር ተያይዞ መከበሩ ድምቀቱን ድርብ ያደርገዋል” አቶ ጥላሁን ደጀኔ

23

ባሕር ዳር: ጥር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ በዓል በደብረታቦር ከተማ በፈረስ ትርዒት በደመቀ ኾኔታ እየተከበረ ይገኛል። የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ “በዓሉ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት እስትንፋስ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱት የእቴጌ ጣይቱ ሐውልት ከተመረቀበት ቀን ጋር መያያዙ ድምቀቱን ድርብ ያደርገዋል” ብለዋል።

በዓሉ በፈረስ ትርኢት ደምቆ መከበሩ ዘወትር እንዲያብብ አድርጎታል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው፤ ፈረስ ከሕዝብ ጋር ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ትውልዱን ለማስተማር በእጅጉ መጥቀሙን አቶ ጥላሁን አውስተዋል። የታሪክ እና የባሕል ቅብብሎሽ አድርጎ ሀገርን በመረከብ ታሪክ የመሥራት ልምድ የሚቀሰምበት ነውም ብለዋል።

ፈረስ ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ ለነጻነት የመታገያ አንዱ ሃብታችን ነው፤ ለአብነትም ዓድዋ ላይ ጣሊያንን በማሸነፍ ታሪክ የተሠራው በፈረስ መሣሪያነት ነው ብለዋል።

ሀገር ሰላም በኾነችበት ጊዜም ፈረስን ከባሕል ጋር አቆራኝቶ ባሕል እና እሴትን የምናስተዋውቅበት ነው። የዛሬው የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ በዓልም መስተጋብርን የምንማርበት ነው ብለዋል።

አቶ ጥላሁን ደብረታቦርን በየበዓላቱ መጎብኘት እና ማድመቅ ብቻ ሳይኾን ሰላማችንን እየጠበቅን፤ በልማትም እየተጋን መኾን አለበት ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመርቆሬዎስ ዓመታዊ በዓል እና የፈረስ ጉግስ ትርዒት ለደብረ ታቦር ከተማ ልዩ መገለጫ ናቸው” የደብረታቦር ከተማ ከንቲባ ደሴ መኮንን
Next article“አጅባር በሰው ተመላች፤ ከዳር ዳር ተጠበበች”