
ባሕር ዳር: ጥር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የፈረስ ጉግስ እሽቅድድምን ከአባቶቻቸው ተቀብለው በበዓለ መርቆሬዎስ በባሕላዊ እና በመንፈሳዊ እሴትን አላብሰው የሚያከብሩት በዓል ስለመኾኑ የደብረ ታቦር ከተማ ከንቲባ ደሴ መኮንን ገልጸዋል፡፡
ከንቲባ ደሴ እምነት እና ባሕል በደብረ ታቦር ይበልጥ ደምቆ የሚታየው በበዓለ መርቆሪዎስ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ በዓሉን ደግሞ የፈረስ ጉግስ ጨዋታ ይበልጥ እንዲደምቅ እንደሚያስችለው አብራርተዋል፡፡
የደብረ ታቦር ከተማ በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ያላት ከተማ መኾኗን ያነሱት ከንቲባው በከተማዋ ያሉትን የቱሪስት መዳረሻዎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ዜጎች እንዲጎበኙ ጋብዘዋል፡፡
ደብረ ታቦር ካሏት በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትወፊቶች በተጨማሪ ለኢንቨስትመንትም ምቹ ከተማ ስለመኾኗ አስረድተዋል፡፡በቆዳ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በብረታብረት፣ በሆቴል ቱሪዝም እና መሰል የኢንቨስትመንት ዘርፎች ምቹ ስለመኾኗም ገልጸዋል፡፡
በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ዜጎች በቂ የሰው ኃይል ያላት ከተማ እንደኾነችም ተናግረዋል፡፡ ደብረ ታቦር ላይ መዋለ ንዋያቸውን ለሚያፈስሱ ሁሉ ከተማ አሥተዳደራቸው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሁሉ አሟልቶ እንደሚጠብቃቸውም አስገንዝበዋል፡፡
ደብረ ታቦር የሰላም ተምሳሌት የኾነች ከተማ መኾኗን ያነሱት ከንቲባው በዓሉ በሰላም እንዲከበር የበኩላቸውን ለተወጡ የጸጥታ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ በዓሉም የሰላም እንዲኾን ተመኝተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!