“ፈረስና ፈረሰኛ፣ ጥበብ እና ጥበበኛ በአጅባር”

38

ባሕር ዳር: ጥር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፈረስና ፈረሰኛ፣ ጥበብ እና ጥበበኛ በአጅባር ተገናኝተዋል። ባቄላ እና ገብስ እያበሉ ፈረሶቻቸውን ያሳደጉ ጀግኖች፣ ከፈረስ ፈረስ መርጠው ያሠገሩ ልበ ሙሉዎች፣ ፈረሶቻቸውን እየሸለሙ አጅባር ላይ ተገናኝተዋል። ከየቀየው ተጠራርተው በመፎካከሪያ ሜዳው ተገናኝተዋል።

“ፈረሱም ሜዳውም ይሄው” ይሉት ብሂል የደረሰ ዛሬ ነው። አጅባር ሜዳ እኔ እቀድም እኔ እቀድም በሚሉ ፈረሶች፣ በጀግንነት ልቆ ለመገኘት በሚፈጥኑ ጀግኖች ተጨንቃለች።

ጥበብ የመላቸው ሊቃውንት በአጅባር በታቦቱ ዙሪያ ተሠድረዋል። ቃለ እግዚአብሔር እንደ ውኃ ይቀዳል፤ ምድሯን ያረሰርሳል። ሊቃውንቱ ድንቅ የኾነውን ሥርዓት እየፈጸሙት ነው።

አጅባር በጥበበኞች፣ በፈረሶች፣ በፈረሰኞች እና በምዕመናን ተሞልታለች። በአጅባር እየኾነ ያለው ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ ድንቅ የፈረስ ጉግስ ትርዒት አይለፈን ያሉ ወጣቶች በአጅባር አራቱም አቅጣጫ ኾነው ታድመውበታል። ይህን የመሰለ ትርዒት፣ ይህን የመሰለ ትዕይንት ፣ ይህን የመሰለ ሥርዓት ማን ሊያልፈው ይፈልጋል? የትም ኾነው ያያሉ እንጂ።

በአጅባር እንኳን ፈረሰኞቹ፣ ፈረሶችም ከሁሉ ልቆ ለመገኘት ትንቅንቅ ላይ ናቸው። ሜዳ ሙሉ እያካለሉ እየተናነቁ ነው። ሁሉም ነገር ድንቅ ነው። በዓላትን ከእነ ሥርዓቱ፣ ሃይማኖትን ከእነ ትውፊቱ ጠብቃ የምታከብረው ደብረታቦር በበዓለ መርቆሪዎስ ትደምቃለች።

አያሌ በዓላት የሚከበሩበት፣ አያሌ ታሪኮችም የተሠሩበት አጅባር ድንቅ ነገር ይታይበታል። የታሪክ እና የሃይማኖት ከተማዋ ዛሬ በበዓለ መርቆሬዎስ ደምቃለች። በውዳሴ፣ በእልልታ፣ ተመልታለች።

በአጅባር ሰማይ ሥር እሴት እየተገለጠ፣ ሃይማኖት እየተሰበከ፣ ታሪክ እየተነገረ ነው። ደብረ ታቦር በበዓለ መርቆሪዎስ የብዙዎችን ቀልብ ትስባለች። ከፍ ከፍም ብላ ትታያለች።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለሕዝባችን ሁለንተናዊ የኾነ አስተማማኝ ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ በቀጣይ መሥራት ይጠይቀናል”
Next articleየፌደራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች ባሕር ዳር ገቡ።