
ባሕር ዳር: ጥር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)እትብታቸው ከተቀበረበት ከታቦር ተራራ፣ ዘውድ እስከደፉት እስከ እንጦጦ ተራራ፣ ከተማ ከመሠረቱበት ከአዲስ አበባ፣ የውጫሌን ውል እስከመረመሩበት እስከ ይስማ ንጉሥ፣ ክተት ከተባለበት ከወረኢሉ ጠላትን ድል እስከመቱበት እስከ ዓድዋ ድረስ ሐውልት ቢሠራላቸው፣ መንገድ ቢሰየምላቸው፣ ትውልድ ሁሉ የጅ መንሻ ቢያቀርብላቸው ያንስባቸው ይኾናል እንጂ አይበዛባቸውም።
ሀገር ላቆሙ ንግሥት ሐውልት ቢቆምላቸው ምን ይገርማል? ነፃነት ላጸኑ እመቤት ማስታወሻ ቢዘጋጅላቸው ምን ይደንቃል? ሕዝብ ላኮሩ እናት እጅ ቢነሳላቸው፣ ትውልድ ሁሉ ቢያረግድላቸው ምን ይገርማል? ስማቸውን መጥራት፣ ለክብራቸው እጅ መንሳት ይገባቸዋልና። እርሳቸው ሀገርን ከእነ ነፃነቷ፣ ከእነ ማንነቷ፣ ከእነ እሴቷ እና ከእነ ሃይማኖቷ አክብረው፣ ጠብቀው አስጠብቀው ለትውልድ አስረክበዋል፣ በቃል ኪዳን አሥረው ለልጅ ልጅ አውርሰዋልና።
ሀገር የሚያጠፋውን የኢጣልያን ወላፈን መከቱት፣ ነፃነት የሚያሳጣውን የሮም መሠሪነት አከሸፉት፣ ዓለምን አንቀጠቅጣለሁ የሚለውን የነጭ ሠራዊት ና ግጠመኝ አሉት፣ ገጥመው ድል መቱት፣ ረጋገጡት፣ በተከበረበት የዓለም ፊት አዋረዱት፣ አሳደዱት፣ የተወለደበትን ቀን አስረገሙት፣፣ የተጓዘበትን ጎዳና አስጠፉት። ከመቃብሩ ላይ ቆመው ከፍ ብለው ታዩበት። ፎክሮ መጥቶ ሳለ ከእግራቸው ስር ጣሉት፣ በሀበሻ ምድር ለነፃነት የማይሰበር፣ ለሀገር ፍቅር የማይበገር ጀግና ጦረኛ እንዳለ አሳዩት። ለሀገራቸው የሚሞቱ ንጉሥ እና ንግሥት እንዳለ አመላከቱት። በሀገር ለመጣ ማንንም እንደማይፈሩ፣ ለማንም እንደማይበገሩ፣ ለማንም እንደማይገብሩ ቅስሙን እና ክብሩን ሰብረው አስረዱት።
በቤት ውስጥ ለባለቤታቸው ዘውድ የኾኑ ብልህ ሚስት፣ በዙፋን ላይ ሩቅ አሳቢ ጠቢበኛ ንግሥት፣ በሀገሩ አጀብ የተባለላቸው የሀገር ብርሃን የሀገር መብራት፣ በጦር ሜዳ አምሳያ የሌላቸው፣ የጦር ስልት የተሰጣቸው ከጦር መሪ የላቁ ጀግኒት፣ በዓለም ፊት ነገን በአሻገር የሚመለከቱ ዲፕሎማት ናቸው። የባርነትን ጨለማ በነፃነት ብርሃን ጋርደዋልና ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ ይሏቸዋል፣ ነፃነትን አስጠብቀዋልና የነፃነት ጠባቂ እያሉ ያወድሷቸዋል፣ መቀነታቸውን ያጠበቁ ደፋር ናቸውና ቆራጧ ንግሥት እያሉ ያሞግሷቸዋል፣ ሀገር እና ሕዝብን በነፃነት አኑረዋልና የነፃነት እናት ይባልላቸዋል ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ።
ምንም አንኳን ሰው መኾን አይቀርምና አፈር ቢቀምሱም፣ ከዙፋን ላይ ባይቀመጡም፣ ዘውድ ደፍተው ባይታዩም፣ በኢትዮጵያ ከሚመጡብኝ አንገቴን እሰጣለሁ ብለው በቁጣ ሲናገሩ ባይደመጡም፣ በፊት እና በኋላቸው፣ በግራ እና በቀኛቸው ታጅበው በሠረገላ ተቀምጠው ባይታዩም፣ በቤተ መንግሥት ባይመላለሱም፣ ዛሬም በትውልድ ልብ ንግሥት ናቸው። ዙፋን የተመቻቸላቸው፣ ክብርና ሞገስ የሚቀርብላቸው።
ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እየተባሉ የሚጠሩት እቴጌ ጣይቱ የትውልድ ሥፍራቸው በበጌምድር፣ በማማው ደብረ ታቦር ነው። ቀኝ አዝማች ታደሰ ዘወልዴ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል አጭር የሕይወት ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ” የጀግና ልቡና ለሀገሬ እንጂ ለራሴ ከሚል ግላዊ ሀሳብ የራቀ ነው። የዕድለኛይቱ፣ ታሪከኛይቱ እቴጌ ጣይቱ ልቡና ለሀገሬ ማለትን ከሁሉ ያስቀድም ነበር” ይላሉ። ቀኝ አዝማች ስለ ንግሥቷ የትውልድ ቦታ ሲጽፉ እቴጌ ጣይቱ በነሐሴ 12 ቀን በ1832 ዓ. ም በጌምድር ውስጥ ደብረ ታቦር በተባለች ከተማ ተወለዱ።
እናታቸው የውብዳር አባታቸው ደግሞ ብጡል ይሰኛሉ። ተጠምቀው ክርስትና የተነሱት በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ነው ብለዋል። በልጅነት ዘመናቸው በዚሁ ደብር ዳዊትን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በጊዜው ይሰጡ የነበሩትን ሌሎች የሃይማኖት ትምህርቶች በየታላላቆቹ አድባራት ተዘዋውረው ተምረዋል። ሕግ እና ሥርዓትን አውቀዋል።
እቴጌ ጣይቱ የግዕዝን ቋንቋ አጣርተው አወቁ። የቤተ መንግሥቱን እና የቤተ ክህነቱን ነገር በደንብ የሚያውቁት በቤት እመቤትነቱም የተዋጣላቸው ነበሩ ይባላል። በማኅደረ ማርያም ኾነው ይማሩ፣ መጻሐፍትን ይቀጽሉ በነበረበት ጊዜ ለቤተክርስቲያን መጋረጃ መሥሪያ በትርፍ ጊዜያቸው ፈትል እየፈተሉ ያቀርቡ ነበር ይባላልና። በበገና ቅኝት እና አደራደርም የተካኑ ነበሩ ብለው ጽፈዋል ቀኝ አዝማች ታደሰ።
እኒህ አስቀድመው ገና ለንግሥና የተዘጋጁ፣ ለቅብዓ መንግሥት የተመረጡ እመቤት በክብር አደጉ። በብልሃት ይመረምራሉ። በጥበብ ይሻገራሉ። ዘመን ነጎደ። ሁለት ታላላቅ ሰዎች የሚገናኙበት ዘመን ቀረበ። ባል እና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ እንዲሉ ሁለት ብልሆች በቃል ኪዳን ሊተሳሰሩ ጊዜው ደረሰ። ንጉሥ ምኒልክ ጠቢቧን ሴት ያገቡ ዘንድ ወደዱ። አስቀድመው ገና ጥበባቸውን እና ብልሃታቸውን የሚያውቁት ንጉሡ እቴጌዋን አግብተው መኖርን ተመኙ። ሁሉም ሠመረ። ታላላቆቹ ተገናኙ።
ቀኝ አዝማች ታደሰ ስለ ጋብቻቸው ሲጽፉ ” የጋብቻቸው ሥነ ሥርዓት ሚያዚያ 25/1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ቅዱስ ቁርባንን ተቀብለው ተፈፀመ” ብለዋል። እቴጌ ከበጌምድር ደብረ ታቦር፣ እምዬ ከሸዋ አንኮበር ተገናኙ። አንድ አምሳል አንድ አካል ኾኑ። እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጎላ ብሎ ከሚነሱ ሴት ነገሥታት መካከል አንደኛዋ ናቸው። ትውልድ ሁሉ በማይረሳው እና በሚዘክረው የዓድዋ ድልም ስማቸው ቀድሞ ይነሳል። ክብራቸው ልቆ ይወሳል። በአንኮበር የተጋቡት እቴጌ እና እምዬ በእንጦጦ ደግሞ ነገሡ።
ተክለፃዲቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በተሰኘው መጽሐፋቸው ” ታላቅ ዳስ እንጦጦ ላይ ተሠርቶ፣ ድግሱ በአይነቱ ተደግሶ፣ በእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን መኳንንቱና መሳፍንቱ ባሉበት ጥቅምት 25/1882 ዓ.ም በጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ተቀብተው በታላቅ ሥነ ሥርዓት ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው የንጉሠ ነገሥትነት ዘውድ ጫኑ። ባለቤታቸው ወይዘሮ ጣይቱ ብጡልም እንደ ደንቡ የንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓተ ንግሥ በተደረገ በሦስተኛው ቀን በጥቅምት 27 ቀን የእቴጌነት ዘውድ ጫኑ” ብለው ጽፈዋል።
እኒህ ታላቅ እመቤት በፖለቲካው ተክነውበታል፣ በወታደሩም ተሰጥተውበታልም፣ ብልሃቱን እና ጥበቡን ከአምላክ ዘንድ ተቀብለውታልና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አያሌ ታሪኮችን ፃፉ። ቀኝ አዝማች ታደሰ የእቴጌ ጣይቱ የፖለቲካ ጥበብ የተከበረ እና ተሰሚነት ያለው ነበር። ዳሩ ግን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳትፏቸው የገነነውና በሀገር አሥተዳደርም ከፍተኛ ሚና መጫወት የጀመረው በውጫሌ ውል ነው ብለዋል። እቴጌ የኢጣልያንን መሠሪነት በመረዳት የውጫሌ ውል እንዲሰረዝ ያ ባይኾን ግን እንደማይስማሙ አሳወቁ። ኢጣልያም መሠሪነቷ በታወቀባት ጊዜ ንጉሡ እና ንግሥቷን ለማግባባት በመልእክተኛዋ አማካኝነት ሞከረች። ንጉሡ እና ንግሥቲቱ ግን አይደረግም፣ አይኾንም አሉ። የሀገራቸውን ክብር የሚነካ ውል እንደማይፈጽሙ አስረግጠው ተናገሩ።
በውጫሌ ውል መፋረስ ሲያጋጥም ንጉሡ እና ንግሥቷ በነፃነት ጉዳይ አይሞከርም ሲሉ የኢጣልያ መልእክተኛ አንቶኔሊ “አንግዲህ ወዳጅነት ቀርቷል፣ ጦርነት ብቻ ነው” ብሎ ሲወጣ ልበ ሙሉዋ ንግሥት እቴጌ ጣይቱ ከት ብለው በመሳቅ ” ጦርነቱን የዛሬ ሳምንት አድርገው፣ በዚህ የሚደነግጥልህ የለም” ብለው በታላቅ ቁጣ መለሱለት በማለት ተክለፃዲቅ መኩሪያ ጽፈዋል። ጦር አልቀረም የውጫሌ ጦር ይዞ መጣ። ንጉሡ ከእቴጌ ጋር መከሩ። ከመኳንንቶቻቸው እና ከጦር አበጋዞቻቸው ጋር ዘከሩ። አዋጅ አስነግረው ወደ ጦር ሜዳ ገሰገሱ። እቴጌም ከባለቤታቸው ጋር ወደ ዓድዋ ዘመቱ።
ወደ ዓድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር አምባላጌ ላይ የኢጣልያን ጦር እንደቆሎ ቅሞት ወደፊት ገሰገሰ። የኢጣልያ ጦርም በመቀሌ መሽጎ ነበር። በዚህም ሥፍራ ብርቱ ውጊያ ተደረገ። በዚህም ውጊያውን በቀላሉ ለማሸነፍ የሚቻልበት እድል ይቀየስ ጀመር። ብልኋ ንግሥትም አንድ ሀሳብ መጣላቸው። በመቀሌ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ሲመለከቱ የነበሩት እቴጌ አንደኛውን መኳንንት መልእክት ያደርስላቸው ዘንድ ላኩት።
ተክለፃዲቅ መኪሪያ ሲጽፉ ” እቴጌ ጣይቱም የድንኳናቸውን መጋረጃ ገልጠው ሲመለከቱ በእርሳቸው አጠገብ አዛዥ ዘ አማኑኤል ቆመው ስለነበር እቴጌይቱ ፊታቸውን ወደ እርሳቸው አዙረው ሒድና ከሊቀ መኳስ አባተ እየተመካከርክ ምንጩን ለመያዝ ትችል እንደኾነ ሞክር ብለው አዘዟቸው። እርሳቸውም ሄደው እንደታዘዙት ከሊቀ መኳስ አባተ ጋር ቢነጋገሩ ሊቀ መኳሱ የምንጩ ሥፍራ ጥልቅና ወደ ኢጣልያኖቹ ምሽግ የቀረበ ነው። በምንጩና በምሽጋቸው መካከል አንድ 150 ክንድ የሚኾን ርቀት አለ። ቢኾንም መተላለፊያውን በመድፍ ሳስጠብቅ ቆይቼ ሌሊት ሲኾን ወታደር ልኬ ምንጩን አስይዛለሁ ብለው መለሱላቸው። አዛዡ ዘአማኑኤል ይኸን መልስ ከሊቀ መኳስ አባተ ተቀብለው ለእቴጌይቱ ቢነግሯቸው በጣም ደስ እንዳላቸው እና ነገሩንም ለአጼ ምኒልክ እንደ አመለከቷቸው ንጉሡም መልካም ነው ብለው ስለመለሳቸው ጽፈዋል።
እስካሁን ድረስ ምሽጉ ውስጥ ገብተን ለመዋጋት ደስታችን ነው ትሉ ነበር። ነገር ግን ወደ ምሽጉ ገብቶ ለመዋጋት እንደዚህ ለበዛችሁት ጦር የምሽጉ መንገድ ጠባብ ስለኾነ ከኢጣልያኖቹ መድፍና ጥይት የበለጠ እርስ በእርሳችሁ ትገዳደላላችሁ። ስለዚህ ሄዳችሁ ጣልያኖቹ ውኃ እንዳይቀዱ ምንጩን ጠብቁ እናንተም እስካሁን ምሽግ ገብተን እንዋጋለን የምትሉትን ያክል የሜዳ ጦርነትን እንደማትፈሩ ተስፋ አለኝ። በዚህ ጦርነት ተዋግተው ለተረፉት ደስ የሚያሰኝ የክብር ሽልማት እሰጣቸዋለሁ። ለሞቱትም ተዝካራቸውን አወጣላቸዋለሁ። ልጆቻቸውንም አሳድግላቸዋለሁ። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን” ብለው አሰናበቷቸው ብለዋል።
የእቴጌይቱን ንግግር የሰሙት ወታደሮች እንደ አራስ ነብር ተቆጥተው ወደ ምንጩ ተጓዙ። እቴጌም ሌሊቱን ሙሉ “አምላኬ ሆይ አታሳፍረኝ እርዳኝ” እያሉ ሲጸልዩ አደሩ። በእርሳቸው ስልት ቀያሽነት፣ በጀግኖች ብርቱ ተዋጊነት ምንጯ ተያዘች። የኢጣልያ ወታደር ጉሮሮው ተዘጋ። ድልም መጣ። የዓድዋ ጦርነትም ጊዜ ደረሰ። ተክለፃዲቅ ስለዚህ ሲጽፉ ዋናው ጦርነት በተጀመረ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ በማጅራታቸው ድንጋይ ተሸክመው በጉልበታቸው ተንበርክከው በጋለ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር። በወታደር በታጠሩት ንጉሠ ነገሥት ላይ የመድፍና የጠመንጃ ጥይት እንደ ዝናብ ይወርድ ነበር።
እቴጌ ጣይቱ ጥቁር ጥላ አስይዘው ዐይነ እርግባቸውን ገልጠው በእግር እየተራመዱ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ በወይዘሮ ዘውዲቱና በደንገጡሮች ታጅበው ወደፊት ጉዟቸውን ቀጠሉ። ወዲያውም የኃላው ወታደር ሲያመነታ አይተው ” በርታ ምን ሆነሀል ድሉ የኛ ነውና በለው” ብለው በተናገሩ ጊዜ ወንድ ሴት ሲያበረታው መሸሽ አይኾንለትምና ሁሉም ወደፊት ገፋ እቴጌይቱ በዚህ ቀን የሴትነት ባሕሪያቸውን ትተው እንደ ወንድ ወታደሮቻቸውን በቀኝና በግራ አሰልፈው ወደ ጦርነቱ ገቡ። መድፈኞቻቸውም በቀኛቸው በኩል ጠምደው እየተኮሱ በመካከል የሚዋጋውን የጠላት ጦር ይመቱ ጀመር ተብሎ ተጽፏል።
እቴጌ በጸሎት፣ ከዚያም በጀግንነት ድል ይመጣ ዘንድ አደረጉ። ነፃነትንም አፀኑ። ጠላትን አሳፍረው ወገንን አኮሩ። በብርሃን ዘመን አኖሩ። እርሳቸው ከተራራ የገዘፈውን ታሪክ ሠሩ። በሥራቸውም ተከበሩ። ከዓድዋ ዘመንም በኋላ ሀገር በማስፋት፣ ሥርዓት በማጽናት፣ ወገን በማኩራት አያሌ ታሪኮችን ጽፈዋል።
ቀኝ አዝማች ታደሰ ሲጽፉ ” እቴጌ ጣይቱ ለምኒልክ ሚስታቸው ከመኾናቸውም በላይ እንደ እህት ኾነዋቸው ስለማናቸውም ነገር ያማክሯቸው ያበረታቷቸው እና ያጽናኗቸው ነበር። ንጉሥ ብለው ነበር የሚጠሯቸው። አጼ ምኒልክም ያከብሯቸው እና ይወዷቸው ነበር። በምክራቸውም ይጸኑ ነበር። ተጋፍተው አያፈርሱትም ነበር” ብለዋል። እኒህ ታላቅ ንግሥት በታሪክ ስመ ገናና ናቸው። የከበረ ታሪክ ሠርተው አልፈዋልና።
ታዲያ ለታሪካቸው ማስታወሻ፣ ለክብራቸው እጅ መንሻ ይኾናቸው ዘንድም እትብታቸው በተቀበረባት፣ ክርስትና በተነሱባት፣ ፊደል በቆጠሩባት ከተማ በደብረታቦር ሐውልት ቆሞላቸዋል። በመነሻቸው ማስታወሻ ተሠርቶላቸዋል። ሐውልታቸውም በልቡ ላነገሳቸው ትውልድ ማስተማሪያ፣ ለእርሳቸውም መዘከሪያ ይኾናል። እቴጌ በአናብስት ተከበው፣ በፈረስ ላይ ተቀምጠው በኩራት ይታያሉ። መቼም ተራማጅ ናቸውና ዛሬም በግርማ የሚራመዱ ይመስላሉ። ክብር ለሚገባው ክብር ይሰጣል። ክብር ይገባቸዋልና ክብር ተሰጥቷቸዋል።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!