በመካከር እና በመግባባት የቀደመ ሰላማችንን እንመልሳዋለን ሲሉ በምስራቅ ጎጃም ዞን የአነደድ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

7

ደብረ ማርቆስ: ጥር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሁሉም አንድ ኾኖ በመቆም፣ በመካከር እና በመግባባት የቀደመ ሰላማችንን እንመልሳዋለን ሲሉ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የአነደድ ወረዳ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ እና በመፍትሔዎቹ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡ ተወያዬቹ በሰላሙ መደፍረስ የሰው ሕይወት ጠፍቷል ንብረትም ወድሟል ብለዋል።

ነዋሪዎቹ የሰላም እጦት ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት፤ ጥፋትም እንዳያስከትል በሰከነ መንገድ በመነጋገር፣ በመመካከር እና በመግባባት ችግሩን መፍታት መቻል አለብን ብለዋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በግብርና ግብዓት ስርጭት እና በሥራ እድል ፈጠራ ሂደቶች ላይ የሚታዩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መንግሥት ማስተካከል እንዳለበትም ነዋሪዎች በውይይታቸው አንስተዋል፡፡

የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ዳግም ጥፋት እንዳይከሰት እና ለከፋ ጉዳት እንዳንጋለጥ ሰላማችንን ማጠንከር ቀዳሚ ተግባራችን ሊኸን ይገባል ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮች የሚያነሷቸው የግብዓት ጥያቄዎችንም በጥንቃቄ እና በተጠና መንገድ ለማሰረጨት እንደሚሠራ ገልጸዋል። ከሥራ እድል ጋር የሚነሳውንም ጥያቄ በጊዜ ሂደት ከሰላሙ ማደግ ጋር ማስተካከል እንደሚቻልም አብራርተዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የ72ኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ገብረ ኪዳን ተስፋየ የአካባቢው ሰላም በአጭር ጊዜ እንዲስተካከል የኅበረተሰቡ ትብብር ማደግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተቀዳሚ ተግባሩ የሕዝብን እና የሀገርን ሰላም መጠበቅ መኾኑን በማመን ሕዝቡ ከሠራዊቱ እና ከሌሎችም የጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመቆም እና አጥፊዎችን በማስተማር ሰላሙን ማስጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረ ታቦር ከተማ በአንድ ግለሰብ የተሠራ የመማሪያ ክፍል ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።
Next articleእቴጌ ጣይቱ በደብረ ታቦር ከተማ ሐውልት ቆመላቸው።