በደብረ ታቦር ከተማ በአንድ ግለሰብ የተሠራ የመማሪያ ክፍል ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።

11

ደብረ ታቦር: ጥር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር በአንድ በጎ ፈቃደኛ ግለሰብ የተሠራ አራት የመማሪያ ክፍል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
የመማሪያ ክፍሉ በታቦር አንደኛ፣ መካከለኛ እና ልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት ነው የተሠራው።

የታቦር አንደኛ መካከለኛ እና ልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ፀጋዬ አስማረ መማሪያ ክፍሎቹ በጭቃ የተሠሩ በመኾናቸው ለመማር ማስተማር የተመቹ እንዳልነበሩ አመላክተዋል።

ከአሁን ቀደም አልማ እና ሌሎች ተቋማት አንዳንድ ሕንፃዎችን መገንባታቸውንም ርእሰ መምህሩ አንስተዋል። የዘመናዊ መማሪያ ክፍሎች መገንባት ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችም ከአሁን ቀደም ባልተመቹ መማሪያ ክፍሎች ይማሩ እንደነበር ገልጸዋል። ያልተመቹ መማሪያ ክፍሎች ለትምህርታቸው አሉታዊ ተጽዕኖ እንደነበራቸው ተናግረዋል።

የመማሪያ ክፍሉን ያሠሩት በጎ ፈቃደኛ አቶ ንጉሤ ክንዴ በትምህርት ቤቱ ያሉ መማሪያ ክፍሎች ደረጃቸውን የጠበቁ አለመኾናቸው ለመሥራት እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል። በትምህርት ቤቱ ተምረው ማለፋቸውን የተናገሩት በጎፈቃደኛው ትምህርት ቤቱ የተጎዳ በመኾኑ እና ለመጪው ትውልድ የተሻለ ነገር ለማድረግ በማሰብ መሥራታቸውን አስታውቀዋል።

“የሠራሁት የተረፈ ገንዘብ ኖሮኝ ሳይኾን ሀገራዊ ግዴታየን ለመወጣት ነው፤ ሁላችንም በተማርንባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት አስተዋጽኦ ልናደርግ ይገባናል” ነው ያሉት። ያሰገነቡት የመማሪያ ክፍል ለአባታቸው መታሰቢያነት መኾኑንም ገልጸዋል።

በጎፈቃደኛው ግለሰብ ለመማሪያ ክፍሉ ግንባታ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገው መገንባታቸውን ነው ያብራሩት። የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን የከተማዋን ልማት የበለጠ ለማሳደግ የባለሃብቶች ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል። ባለሃብቶች ለከተማ ልማት ሚናቸው ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል።

በከተማዋ የሚወጡ ባለሃብቶችን በመደገፍ እና በመንከባከብ የከተማዋን ልማት ማፋጠን እንደሚገባም ከንቲባው አመላክተዋል። ባለሃብቱ ያደረጉት ተግባር በታሪክ የሚታወስ ታላቅ ሥራ መኾኑንም ገልጸዋል። በጎ ፈቃደኛው ላደረጉት እና ትውልድ ለማይዘነጋው አበርክቷቸው ከንቲባው ምሥጋና አቅርበዋል።

የተገነባውን የመማሪያ ክፍልም የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ክፈተው፣ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረታቦር – የድንቅ ባሕል እና ታሪክ ባለቤት ምድር!
Next articleበመካከር እና በመግባባት የቀደመ ሰላማችንን እንመልሳዋለን ሲሉ በምስራቅ ጎጃም ዞን የአነደድ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡