ደብረታቦር – የድንቅ ባሕል እና ታሪክ ባለቤት ምድር!

23

ባሕር ዳር: ጥር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በየዓመቱ ጥር 25 በፈረስ ጉግስ ትዕይንት እና በሌሎች ባሕላዊ ሁነቶች ደምቆ በደብረታቦር ከተማ የሚከበረው የመርቆሬዎስ በዓል የማይረሳ እና የተመልካችን ቀልብ የሚይዝ ልዩ ውበት ነው።

ዛሬ በርካታ ፈረሰኞች ሰጋር እና ሽምጥ ጋላቢ ፈረሶቻቸውን አሳምረው በመሸለም ከየአቅጣጫው በመሰባሰብ አጅባር ሜዳ ላይ ይገናኛሉ። ይህንን ትዕይንት የናፈቁ ሁሉ አይተው ለመደመም በአጅባር ሜዳ ይከትታሉ።

በአጅባር ሜዳ የተገኘ ሁሉ አንድም ፈረሰኛውን ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ ይዘክራል፤ ሁለትም የቀድሞ ጦረኛ አርበኞችን ታሪክ ለማስታወስ የሚካሄደውን የፈረስ ጉግስ ፍልሚያ አይቶ መንፈሱን ያድሳል።

በዚህ ዕለት ዓመቱን ያድርሰን ተባብሎ በፍቅር ይመረቃል፤ ታቦቱ በስዕለት ይታጀባል። ቆንጃጅቶችና ኮበሌዎች በውብ ባሕላቸው ደምቀው እንግዶቻቸውን ይቀበላሉ፤ በሆታና በእልልታ በታጀበው ጨዋታቸው የዓመት ትዝታን ይሰንቃሉ። እንግዳ ተቀባይ ነዋሪዎችም ቤታቸውን አዘጋጅተው የመጣውን ሁሉ “ኖሩ” ይላሉ።

በተዋቡ ፈረሶች እና በኩሩ ፈረሰኞች በሚደምቀው የመርቆሬዎስ ዓመታዊ በዓል በታሪካዊቷ ደብረታቦር ተገኝቶ መታደም ልብን በሐሴት ይሞላል፤ የአካባቢውን ሕዝብ ባሕል፣ እሴት እና ታሪክ ከጥሩው ቀድቶ ለመረዳትም እድል ይሰጣል። ዛሬ በደብረታቦሩ አጅባር ሜዳ መገኘት መታደል ነው – ያ ቦታ የድንቅ ባሕል፣ እሴት እና ታሪክ ባለቤት ነውና!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ13 ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ሃብታቸውን ማስመዝገባቸው ተገለጸ፡፡
Next articleበደብረ ታቦር ከተማ በአንድ ግለሰብ የተሠራ የመማሪያ ክፍል ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።