
ደብረ ብርሃን: ጥር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ደብረብርሃን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሙስናን ለመከላከል በተሠራው ሥራ ከ13 ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ማስቻሉን ገልጿል። የአማራ ክልል መንግሥት ለሙስና ተጋላጭ የኾኑ የሥራ መስኮችን በመለየት የሃብት ምዝገባ እንዲካሄድ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
አሠራሩ ግለጽነት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማስቻል ታሳቢ ተደርጎ የመንግሥት ሠራተኞች የሃብት ምዝገባ እንዲካሄድ በአዋጅ ቁጥር 187/2003 ወሳኔ በማሳለፍ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የደብረብርሃን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሃብት ማሳወቅ እና ማስመዝገብ ቡድን መሪ ራሄል ወርቁ የመንግሥት ተሿሚዎች፣ ተመራጮች እና የመንግሥት ሠራተኞች ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የወጣዉ አዋጅ ያስገድዳል ብለዋል። ሃብት እንዲያስመዘግቡ ተጠይቀው ኾን ብለው የማያስመዘግቡ ግለሰቦች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው 1 ሺህ ብር በመክፍል ሃብት እንዲያስመዘግቡ አሊያም እንደ ሙስና ተጋላጭነታቸው ክብደት እና ቅለት ታይቶ እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ አዋጁ እንደሚያስገድድም ነው ያስገነዘቡት።
የሃብት ማስመዝገብ ሂደቱ በየሁለት ዓመት ተኩል እንደሚታደስ ያነሱት ቡድን መሪዋ የሙስና ወንጀል ሲፈጸም ዜጎች በስልክ ቁጥር 011 637 59 64 በመደወል አለያም በሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር በደብረብርሃን ከተማ ባለው መሥሪያ ቤት በአካል በመገኘት ጥቆማ መስጠት እንደሚቻልም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ፋንታነሽ መሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!