
ባሕር ዳር: ጥር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በየዓመቱ ጥር 25 በቁምነገረኞች ቀየ፤ በተለይም ከዴንሳ ተራራ ግርጌ ለዐይን እንግዳ የኾነ ልዩ የፈረስ ትርኢት ይታያል።
እነዚያ የእስቴ ፈረሰኞች ፈረሳቸውን ሸልመው ከጥናፋ፣ ዳት ጊወርጊስ፣ አጭቃን ኪዳነ ምሕረት፣ ቆማ ፋሲለደስ እና ሌሎችም አካባቢዎች ተሠባሥበው የዋንቃ ወንዝን ይሻገራሉ፤ ከአምሳለ አንበሳው ተራራ ግርጌ በአንቦ ሜዳ ይከትታሉ።
ጀግኖች ከነፋስ የሚፈጥኑ ፈረሶቻቸውን እየኮለኮሉ አባቶቻቸው ጠላትን እንዴት ይዋጉ እንደነበር ለልጆቻቸው ያሳያሉ። በዚያ የተገኘ ሁሉ የተለያየ የፈረስ ትዕይንት ተመልክቶ ለመንፈሱ ምግብ ያተርፋል።
የቅዱስ መርቆሬዎስ ታቦተ ሕግ በዋንቃ ወንዝ ዳርቻ ወርዶ ያድራል። እስቴ የበርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መፍለቂም ናት። ቀሳውስቱ እና ሊቃውንቱ ልዩ በኾነው የቆሜ ዜማ እና ዝማሜ ቀኑን ልዩ ያደርጉታል። ይህ ትዕይንትም በእስቴ ብቻ የሚደምቅ ሁነት ነው።
እስቴ እንግዳ ተቀባይ ነዋሪዎች፣ በጥቅሻ እየተግባቡ ባሕል እና ወጋቸውን ለማሳመር የሚተባበሩ ወጣቶች አሏት። በእስቴዎች እንግዳ ተቀብለው በወጉ ማስተናገድን ሲያውቁበት ለጉድ ነው። ለዚያም ይመስላል:-
“ያንች ሀገር ወዴት ነው – የኔስ ሀገር እስቴ፣
ብሉልኝ ጠጡልኝ – የሚለው በሞቴ” ተብሎ የተዘፈነላቸው።
ጥር 25 ደንሳ እስቴ መካነ ኢየሱስ ዘልቆ የመርቆሬዎስ ዓመታዊ በዓል ማክበር ብዙ ትርፍ አለው። በዚህ ቀን በመካነ ኢየሱስ መገኘት የታታሪዎችን ባሕል እና እሴት በቦታው ተገኝቶ ለመመልከት እና የጀግኖችን የፈረስ ትርኢት ታድሞ ደስታን ለመሸመት ያስችላል።
የተኛ አንበሳ ቅርጽ በመያዙ “አምሳለ አንበሳው” እየተባለ የሚሞካሸውን የዴንሳ ተራራ ቅርጽ በቅርበት ተመልክቶ የተፈጥሮን ነገር ለማድነቅም በእስቴ መካነ ኢየሱስ መገኘት ያስፈልጋል።
መልካም በዓል!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!