
ባሕር ዳር: ጥር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በቅርቡ ድርጅቱን ለኪሳራ ዳርገው በነበሩት 42 ሺህ ሜትሪክ ቶን የመጫን አቅም ባላቸው ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የቀየራት ዓባይ ፪ 60 ሺህ ቶን ኤን ፒ ኤስ የአፈር ማዳበሪያ ጭና ጅቡቲ ገብታለች።
ቀደም ሲል በውጭ ሀገራት መርከቦች ኪራይ ሲከናወን የነበረው የአፈር ማዳበሪያ ጭነት ቀይ ባህር አካባቢ ከተከሰተው የደኅንነት ስጋት አኳያ ወደ አካባቢው ላለመጓዝ በመወሰናቸው የተነሳ ችግር ላይ ይወድቅ የነበረውን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ተግባር በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ መርከብ ዓባይ ፪ ማጓጓዝ ተችሏል።
ይህን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ጅቡቲ ወደብ የማጓጓዝ ሥራ አብዛኛውን የዩሪያ ማዳበሪያ ዓባይ ፪ የምትጓጉዝ ሲሆን በቀይ ባሕር አካባቢ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ሊያጋጥም ይችል የነበረውን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሥራ ከማስተጓጎል የታደገ ነው።
ዓባይ ፪ በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ በግዙፍነቱ አቻ የለሽ የሆነች እና የባሕር ትራንስፖርት ሥራውን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው።
በ3 ሺህ ቶን የመጫን አቅም ባላቸው መርከቦች ሥራውን የጀመረው የባሕር ትራንስፖርት 13 ሺህ፣ 18 ሺህ፣ 25 ሺህ እያለ ከ 5 እስከ 10 ባልዘለለ የዕድገት ጥግግት ፍሬ እያፈራ እነሆ በአስገራሚ እጥፋት 63 ሺህ 229 ቶን የመጫን አቅም ደርሶ ለሀገር በረከት እና የቁርጥ ቀን መኩሪያ ኾኗል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!