
ባሕር ዳር: ጥር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ተፈጥሮ በሞሸረው፣ በአምበሳ አምሳል በተፈጠረው፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ በደራረበው ሥፍራ የከበረ ነገር ሞልቷል። ቅዱሳን አባቶች ይኖሩበታል፣ ባሕታውያን ይመላለሱበታል፣ የበቁ አባቶች ፈጣሪን ያመሠግኑበታል። ሊቃውንቱ ይፈልቁበታል፣ ወንበር ዘርግተው ያስተምሩበታል፣ ደቀመዛሙርቱ ከሊቃውንቱ እግር ሥር ተቀምጠው እውቀትን ይቀዱበታል፣ ሥርዓትን ይማሩበታል፣ ሕግን ያውቁበታል፣ ሃይማኖትን ያጸኑበታል።
በዚያ ምድር ለአምላክ ምሥጋና ሳይደረስበት፣ ለምድር ሰላምና ፍቅር ሳይለመንበት፣ አምላክ በረከት እና ረድኤት ይሰጥ ዘንድ ሳይማጸኑበት ውሎ አይታደርም። ደጋጎቹ ይጠለሉበታል፣ ስጋቸውን እያደከሙ ነፍሳቸውን ያበረቱበታል፣ ከአላፊዋ ዓለም እየራቁ ወደ ማያልፈው ዓለም ይጠጉበታል፣ የሰማይ አባታቸውን ትዕዛዝ ያከብሩበታል። የሰማይ አባታቸውን ክብር ይገልጡበታል።
በዚያ ምድር ምስጢር የጠለቁ ሊቃውንት፣ ሕዝብን የሚባርኩ ጳጳሳት፣ ለአገልግሎት የሚፋጠኑ ዲያቆናት፣ ወጥተውበታል፣ ሀገር የሚገዙ ነገሥታት እጅ ነስተውበታል፣ በዚያው አርፈው አምላክ ጥበብ ይሰጣቸው ዘንድ ተማፅነውበታል፣ የእጅ መንሻ ስጦታ አቅርበውበታል፣ ለስማቸው ማስታወሻ ይኾን ዘንድ አሻራቸውን አሳርፈውበታል።
ከፈረስ ፈረስ መርጠው የሚያሳድጉ ፈረሰኞች በግርማ ይታዩበታል፣ በጀግንነት ይመላለሱበታል። በአሸናፊነት ይደምቁበታል። ያልተበረዘች ባሕላቸውን፣ ከእነ ክብሯ ያለች እሴታቸውን ያሳዩበታል። በክብርም ይጠብቁበታል። ፈረሶቻቸውን ሸልመው፣ እነርሱም ለጉግስ በተመቸው ልብስ ተሸልመው፣ ዘንጋቸውን አስተካክለው በአንበሳ አምሳል ከተሠራው ተራራ ግርጌ ሜዳ እያካለሉ ሽምጥ ይጋልባሉ። አንደኛው ከሌላኛው ልቆ ለመገኘት ፈረሶቻቸው ይተናነቃሉ። ሠጋሪዎቹም ፈረሶቻቸውን እየኮለኮሉ ሜዳ ሙሉ ያካልላሉ። በዚያ ምድር ሃይማኖት እና እሴት በአንድ ላይ ጸንተው ይታያሉ፣ ጀግንነት እና እንግዳ ተቀባይነት ከፍ ብለው ይኖራሉ እስቴ ዴንሳ መካነ ኢየሱስ።
በዓለ መርቆሬዎስ ደርሷልና ሜዳው ተውቧል። ፈረሶቹ ይሸለማሉ፣ ፈረሰኞቹ ይዋባሉ፣ ልቀው ለመገኘት ከየቀየው ይወጣሉ። ሊቃውንቱ ያማረውን ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰው ያማረውን ሥርዓት ይፈጽማሉ። ወይዛዝርቱ ደምቀው ይታያሉ፣ ጎበዛዝቱ በአማረ ግርማ ይገማሸራሉ። በበዓለ መርቆሬዎስ እስቴ መካነ ኢየሱስ ልዩ ነውና።
የካልዒት እስክንድርያ ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን የድጓ መምህር እና የቤተክርስቲያኑ አሥተዳዳሪ መላከ ሃይማኖት ሲሳይ አሰፋ ስለ ታላቁ ደብር አመሠራረት ሲነግሩን ያ ሥፍራ አስቀድሞ ገና የአድያም ሰገድ ኢያሱ የጉልት ቦታቸው ነበር። አድያም ሰገድ ኢያሱ በዚያ ሥፍራ 150 ባዝራዎችን ያረቡበት ነበር። የሚያረቧቸው ባዝራዎች እሳቸው እና መኳንንቶቻቸው፣ መሳፍንቶቻቸው፣ የጦር አበጋዞቻቸው ዳገት የሚወጡባቸው፣ ቁልቁለት የሚወርዱባቸው፣ በሜዳ የሚጋልቧቸው ነበሩ። ምን ይሄ ብቻ ጦር ሜዳ የሚወርዱባቸው፣ በጠላት መካከል ጎራዴና ጋሻ ይዘው የሚዋጉባቸው ጭምር ናቸው እንጂ።
አድያም ሰገድ አራት ሹሞችን ሹመው ባዝራዎችን ያረባሉ። እንደዛሬው በመሬት መሽከርከር ፣ በሰማይ መብረር የለምና ጉዞው ሁሉ በፈረስ ነበር። ንጉሡም መንገዳቸው የተቃና ይኾን ዘንድ ነበር ፈረሶችን የሚያረቡት። በሹም የሚያስጠብቁት። ሊቁ ሲናገሩ ታላቁ ንጉሥ አድያም ሰገድ ኢያሱ በዚያ ሥፍራ ቤተክርስቲያን የማሳነጽ ሕልም ነበራቸው። ቤተክርስቲያን አሳንጸው ኪዳን ሲደረስበት፣ ቅዳሴ ሲቀደስበት፣ ስጋ ወ ደሙ ሲፈተትበት ለማየት ያልሙ ነበር። ዳሩ ያለ ፈቃድ የሚፈፀም የለምና ቤተክርስቲያን ሳያሳንጹ ዘመናቸው ተቋጨ።
በዚህ ሥፍራ የመናኔ መንግሥት እየተባሉ የሚጠሩት አጼ ዮሐንስ (ፃዲቁ ዮሐንስ) ጊዜያዊ የጸሎት ቤት እንደነበራቸውም ይነገራል። እኒያ ፃዲቅ ንጉሥ ከቤተመንግሥታቸው ርቀው ወደዚያ በሄዱበት ጊዜ በዚያ ሥፍራ እያደሩ ጸሎት ያደርሱበት፣ አምላካቸውን ይማጸኑበት ነበር ይባላል። ዓለምን የናቋት፣ የማታያቸው እና የማያዩዋት አባቶችም ቅጠል ለብሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው በጸሎት ይኖሩበት እንደነበርም ይነገራል።
በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የታሰበው ቤተ መቅደስ በአጼ ተክለ ጊዮርጊስ (ፈፃሚ መንግሥት) ዘመነ መንግሥት ታነጸ። ይህም ዘመን 1772 ዓ.ም ነበር። በዚህ ዘመን ደጅ አዝማች ኃይሉ እሸቴ የተባሉ መስፍን የንጉሡ የቅርብ ሰው ነበሩ። እኒህም ሰው ሕዝብ ሁሉ የሚወዳቸው እና የሚያከብራቸው ነበሩ። በዚህም ጊዜ የአድያም ሰገድ ኢያሱ ጉልት በነበረው ሥፍራ ቤተክርስቲያን ያሠሩ ዘንድ ወደዱ። አምላክ በዚያ ሥፍራ ስሙ የሚመሰገንበት ቤተ መቅደስ ይታነጽበት ዘንድ ወዷልና።
ደጅ አዝማች ኃይሉ እሸቴ ይህን ቤተክርስቲያን ከመሥራታቸው አስቀድሞ አምላክ ፈቃዱን ይሰጣቸው ዘንድ ሱባኤ ያዙ ይባላል። በጸም እና በጸሎት በርትተው አምላካቸውን በለመኑት ጊዜ ታላቅ የግራር ዛፍ ታገኛለህ። ያ የግራር ዛፍም ዙሪያው በደን የተከበበ ነው። ግራሩን ስትቆርጥም የበቃ ቅዱስ ሰው አጽም ታገኛለህ። የቅዱሱን አጽምም ሠብሥበህ በሳጥን አድርገህ ቅበረው። ቤተክያኑንም እዚያ ላይ ሥራው። የታቦቱን ማረፊያ መንበሩንም ከቅዱሱ አጽም ላይ አድርገው። ያም ቤተክርስቲያን ሃይማኖት የሚጸናበት ዘወትር የፈጣሪ ነገር የሚነገርበት፣ ሊቃውንት እና ደቀመዛሙርት የማይታጡበት፣ ጳጳሳት የሚወጡበት ታላቅ ቦታ ይኾናል ተባሉ። የተባሉትን አንድም ሳያስቀሩ ፈጸሙ።
በተሠራው ቤተ መቅደስም ታቦተ ኢየሱስን አስገቡ። ለቤተክርስቲያኑ የሚያገለግሉ 150 ሊቃውንትን መደቡ። ይሄም 150 ፈረሶች ሲረቡበት በነበረበት 150 ሊቃውንት የሚያገለግሉት ደብር ተደበረ። ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ። ሁሉም በምሳሌ እና በምስጢር ኾነ።
ሊቁ እንደሚሉት የአድያም ሰገድ ኢያሱ ጉልት የነበረው ቦታ የምድራዊ እና የሰማያዊ የዘላለማዊ ንጉሥ የኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን መቀመጫ ኾነ። ሊቁ መካነ ኢየሱስ የተዋሕዶ እምነት የነገሠበት፣ ሃይማኖት የጎደላቸው፣ ሥርዓት ያነሳቸው ሰዎች ያልረገጡት፣ በዓይናቸውም ያላዩት ቅዱስ ሥፍራ ነው ይሉታል። ደብረ ሃይማኖት የተባለበትም ሃይማኖት የጸናበት፣ ሥርዓት የከበረበት፣ ሕግ የተከበረበት ሥፍራ ስለኾነ ነው ይላሉ።
አስቀድሞ በራዕይ እንደተነገረ በዚህ ሥፍራ ደብር ከተደበረ፣ ሥርዓት ከተሠራ ጀምሮ መምህራን ወንበር አልተውበትም፣ ቃል ከመንገር አላቆረጡበትም፣ የመጻሕፍት፣ የድጓ መምህራን አልተለዩትም ይላሉ ሊቁ። በዚያ ታላቅ ደብር ጳጳሳት ተምረው ወጥተውበታል። ጉባኤ አልታጎለበትም። አስቀድሞ እንደተነገረ ስሙ ከፍ እንዳለ እውቀት እንደፈሰሰበት፣ ጥበብ እንደፈለቀበት፣ ምስጢር እንደተሜሰጠረበት ይኖራልና።
ንጉሠ ነገሥታት ዘውዲቱ በክርስትና ስማቸው አስካለ ማርያም ለታላቁ ደብር ንዋየ ቅድሳትን አበርክተዋል። በዙፋን ላይ የተቀመጡት ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ ከአንድም ሁለት ጊዜ ታላቁን ደብር አሠርተውታል። አጼ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት በኾኑበት ዘመን ደጅ አዝማች ኃይሉ እሸቴ ያሠሩት ቤተክርስቲያን አርጅቶ ነበር። አጼ ኃይለ ሥላሴ በነገሡ ዘመን ቤተክርስቲያኑን ማሠራት ጀመሩ። ሕንፃ ቤተክርስቲያኑም ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ዘመን የኢጣልያ ወረራ መጣ። ሁሉም ነገር ወደ ጦር ሜዳ ኾነ። ታሪክና ሃይማኖት ለማጥፋት የምትታትረው ኢጣልያም በ1930 ዓ. ም አቃጠለችው።
የኢጣልያ ሠራዊት አድባራትን እና ገዳማትን ሲያቃጥል ስለነበር ሊቃውንቱ ታቦታቱን እና ንዋየ ቅዱሳቱን ይዘው ወደ ዋሻ ማርያም ሄደው ተጠለሉ። መልካም ዘመን እስኪመጣ ድረስ በዚያው ቆዩ። ኢጣልያ ተሸንፋ ከተባረረች በኋላም ሊቃውንቱ ወደ ቀደመ ሥፍራው መለሱት። በዚያም ሥፍራ በመቃረቢያ ለዓመታት ኖረ። ንጉሡን እንደገና ያሠሩት ዘንድ ወደዱ። እየተሠራ ባለበት ጊዜም ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ደብሩን ያዩ ዘንድ መጡ። እሳቸው በመጡ ጊዜ የሀገሬው ሰው በእልልታ እና በኾታ ተቀበላቸው፣ ሊቃውንቱ በዝማሬ አጀቧቸው። ሥራውንም ተመለከቱ። የደብሩን አሠራር ከተመለከቱ በኋላ ወደ ደብረታቦር ተመልሰው ግብር አበሉ።
በዚህ ሥፍራ ድንቅ ታሪክ አለ። በ1930 ዓ.ም በተቃጠለ ጊዜ ካህናቱ ታቦታቱን ሲያሸሹ ከዝሆን ጥርስ እና ከወርቅ የተሠራ የታቦት ማረፊያ ነበር። ካህናቱም ንዋየ ቅድሳቱን ባሸሹ ጊዜ ያን የታቦት ማረፊያ ረስተውት ነበር። ሀገር ሰላም ኾኖ በተመለሱ ጊዜ ጥምቀት ደርሶ ታቦቱን ከመንበሩ ሊያወጡ ሲሉ የታቦቱ ማረፊያ አልነበረም። ረስተውት ሄደው አብሮ ተቃጥሎ ነበር። ካህናቱም የት እናሳርፈው እያሉ ተጨነቁ። ከብዙ ጭንቀት በኋላም የታቦት ማሳረፊያ ለማበጀት ወደ ሜዳው በወረዱ ጊዜ የሰው እጅ ያልሠራው አምሮ የተሠራ ድንጋይ በተመረጠ ሥፍራ ላይ ተቀምጦ አገኙ። በዚህም ጊዜ የፈጣሪ ፈቃድ ኾኗል ብለው ደስ ተሰኙ። ታቦቱንም በክብር አምጥተው በዚያው አሳረፉ። ታቦቱ ዛሬም ድረስ በወረደ ጊዜ በተቀመጠው ድንጋይ ላይ ያርፋል ብለውናል ሊቁ።
በዚህ ሥፍራ በዓለ መርቆሬዎስ በድምቀት ይከበርበታል። ይህም ታቦት ቤተክርስቲያኑ በታነፀ ጊዜ ከኢየሱስ ታቦት ጋር መግባቱን የኔታ ነግረውናል። በበዓለ መርቆሬዎስ የጥናፋ፣ የፋርጣ እና የእስቴ ፈረሰኞች ከፈረስ ፈረስ መርጠው ይገናኙበታል። አንደኛው ከሌላኛው ልቆ ለመገኘት ይፎካከሩበታል። ጀግንነታቸውን ያሳዩበታል። ቅልጥፍናቸውን እና ብልሃታቸውን ይገልጡበታል። ፈረሰኞቹ አንደኛው ከሌላኛው ልቆ ለመገኘት ሲፎካከሩ በሜዳው የመላው ሁሉ በጉጉት ይመለከታቸዋል። ይደነቅባቸዋል። ያሞግሳቸዋል።
ሊቃውንቱ እጹብ ድንቅ የሚያሰኘውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይፈጽማሉ። ሥርዓቱ ተፈጽሞ ታቦቱ ወደ መንበሩ ሲመለስ ከሰባት ቦታ ላይ ያርፋል። ይሄ ሥርዓት አይታጎልም። ይሄም የሰባቱ ሚስጥራት ምሳሌ ነው። የኔታ ሲነግሩን በመካነ ኢየሱስ ያለ ምክንያት እና ያለ ምሳሌ የሚፈጸም አንድም ነገር የለም። ሰባቱም ምሳሌዎች የሰባቱ ማዕረገ ቤተክርስቲያን፣ የሰባቱ እለታት እና የሌሎች ምስጢራት ምሳሌ ነው።
ሊቁ እንደሚሉት አምላክ ከሠራው ሕግ አንዱ አትግደል ነው። መገዳደልን እግዚአብሔር አይወደውም።መጋደሉን ትተን መተሳሰቡን፣ መተዛዘኑን፣ መቀራረቡን፣ መጣላቱን ትተን መፋቀሩን፣ መራራቁን ትተን መቀራረቡን፣ መለያየቱን ትተን አንድ መኾኑን እንምረጥ፣ እርሱን ገንዘብ እናድርግ ። የሰው ልጅ መኝታው ሰላም ነው፣ መንገዱ ሰላም ነው፣ ሀሳቡም ሰላም ነው፣ ሞቱም ሰላም ነው። መብሉም ሰላም ነው፣ መጠጡም ሰላም ነው፣ ሰላም ከሌለ ሞቶም በክብር መቀበር ይቀራልና ሰላም ፈጥራችሁ ወደ ተቀደሰው ቦታ ኑ። የተቀደሰውን ቤት ተመልከቱ። የአምላክን ሥራም አድንቁ ነው ያሉት። ምድርን በደም አናርክሳት፣ በሰላም እንምላት እንጂ ይላሉ ሊቁ። በዚያ ሥፍራ ነገሥታቱ የሰጧቸው ስጦታቸው እና የከበሩ ንዋዬ ቅድሳት ይገኙበታል።
ሊቃውንቱ ወደ ሚፈልቁበት ፣ ፈረሰኞቹ ወደ ሚገኙበት ፣ የከበረ ታሪክ ወደ መላበት፣ ቅዱሳን አበው ወደ ማይጠፉበት፣ እሴት እና ባሕል ወደ አልተበረዘበት ወደዚያ ታላቅ ቦታ ተጓዙ። እግራችሁ መልካሙን ምድር ትረግጣለች። እጃችሁ የተቀደሰውን ትዳብሳለች፣ ዓይናችሁ የተዋበውን ታያለች። ጀሯችሁ እጹብ የሚያሰኘውን ትሰማለች፣ አፍንጫችሁ ሀሴት የሚሰጠውን እጣን ታሸትታለች፣ ነብሳችሁ ትረጋጋለችና።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!