ዓመት ሙሉ አምራች የኾነውን የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ሰላም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መኾናቸውን የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር የጸጥታ አካላት ገለጹ።

13

ባሕር ዳር: ጥር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በአምስት ከተማ እና በአራት ወረዳ አሥተዳደሮች የጸጥታ አካላት ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
በሥልጠናው የፖሊስ፣ የሚሊሻ፣ የሰላም አስከባሪ አመራሮች እና አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በዳንሻ ከተማ አሥተዳደር የሥልጠና ማዕከል ያገኘናቸው ሠልጣኝ የጸጥታ አባላት የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ዓመቱን ሙሉ አምራች መኾኑን አንስተው የአርሶ አደሩ ምርታማነት እና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የአካባቢያቸውን ሰላም በቁርጠኝነት እያስጠበቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ከሥልጠናው እውቀት እና ልምድን እያገኙ መኾኑንም ተናግረዋል።

የዞኑ ሕዝብ ከራሱ አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሚኾን ምርታማነትን እያረጋገጠ እንደሚገኝ ገልጸው በዞኑ እየተካሄደ የሚገኘው ዘርፈ ብዙ ልማት እንዲቀጥል እና ኅብረተሰቡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ማልማት እንዲችል በቀጣይም የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ ቀን ከሌሊት እንደሚተጉ አረጋግጠዋል።

በሥልጠናው የተገኙት የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አቡዱልውኀብ ማሞ የጸጥታ አካላቱ በአመለካከት በክህሎት እና በእውቀት በቂ ልምድን እንዲያገኙ የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለጸጥታ አካላት የፖለቲካዊ እና የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና መሰጠቱ የአካባቢን ሰላም ለማረጋገጥ ወሳኝነት አለው ያሉት ከንቲባው ዘርፈ ብዙ ብቃት ያለው የጸጥታ አካል ለመፍጠር ሥልጠናው ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ማሠልጠኛ ማዕከል አሥተባባሪ ደጋለም ሲሳይ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ለሦስት አስርት ዓመታት የሰላም እና የነጻነት አየር በማጣቱ የሰላም እጦት የሚያሰከትለውን ጉዳት ስለሚያውቅ የአካባቢውን ሰላም በቁርጠኝነት እየጠበቀ ነው ብለዋል።

ከለውጥ ማግስት ያገኘውን ነጻነት እና ሰላም ይጠብቃል፤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ከሚለቀቁ ሃሰተኛ መረጃዎች እና የአካባቢን ሰላም ከሚያውኩ ጉዳዮች ራሱን በማራቅ ሰላሙን እያረጋገጠ መኾኑን ተናግረዋል።

ለጸጥታ አካላት እየተሰጠ የሚገኘው ሥልጠና ለሕዝብ ታማኝ እና ለሕገ መንግሥት ተገዥ የኾነ ውስጣዊ አንድነትን የሚያረጋግጥ ጠንካራ የጸጥታ አካል ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል። ሠልጣኝ የጸጥታ አካላት ሥልጠናውን በትኩረት በመከታተል የኅብረተሰቡን ሰላም እና ነጻነት አስጠብቆ ለመዝለቅ ቁርጠኛ ሊኾኑ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ዘጋቢ – ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ታቦር ጎዳናዎቿን አስውባ፤ እልፍኞቿንም አሳምራ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው።
Next article“ሊቃውንቱ የሚፈልቁበት፤ ፈረሰኞቹ የሚገኙበት”