ደብረ ታቦር ጎዳናዎቿን አስውባ፤ እልፍኞቿንም አሳምራ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው።

10

ባሕር ዳር: ጥር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪካዊቷ ከተማ ደብረ ታቦር ለበዓለ መርቆሬዎስ ድግሷን ደግሳለች፣ ጎዳናዎቿን አስዋበለች፣ እልፍኞቿን አሰማምራለች። ጎደናዎቿ በተወዳጁ የሀገር ቀለም በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ አሸብርቀዋል። ዘወትር ግርማ የማይለያቸው አብያተ ክርስቲያናቱም በሀገር ሠንደቅ ተጎናፅፈዋል።

ከጥር 10 ጀምሮ እስከ ጥር 29 ድረስ ድግሶችን የምትደግሰው፣ ታቦታትን የምታከብረው፣ ሃይማኖት እና እሴትን የምታፀናው፣ ታሪክን የምትነግረው ደብረ ታቦር በዓለ መርቆሬዎስንም ለማክበር ተዘጋጅታለች።

ደብረ ታቦር በበዓለ መርቆሬዎስ በእልልታ ትሞላለች፣ በሆታ ትጨነቃለች፣ ከሰማይ የወረዱ እርግቦች በመሰሉ ምዕምናን ታጌጣለች፣ አስደንጋጭ ግርማ ባለቸው ፈረሰኞች ትሞሸራለች።

በታሪክ የተሞላች፣ እርሷም ታሪክ የሆነች፣ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናትን አቅፋ የያዘች በበዓለ መርቆሬዎስ ትደምቃለች። ፈረሰኞቹ፣ ሊቃውንቱ፣ ዲያቆናቱ፣ ካህናቱ፣ መነኮሳቱ፣ ወይዛዝርቱ እና ጎበዛዝቱ ያስውቧታል።

ታላቁ እና ታሪካዊው አጅባር ሜዳ ደግሞ ታቦታቱ ያርፉበታል። ፈረሰኞቹ ይሠግሩበታል። እነሆ በዓለ መርቆሬዎስ ደርሷልና የቴዎደሮስ የዙፋን መቀመጫ፣ ደብረ ታቦር ድግሷን ደግሳለች። ደጋጎቹ እልፍኛቸውን አሰማምረው፣ ጠጅና ፍርንዱሱን ጥለው፣ እንጀራውን ጋግረው ለእንግዶቹ አሰማምረውታል።

“ስሞት አፈር ስሆን” እያሉ ማብላት እና ማጠጣት፣ ከአልጋ ወርደው እንግዳ ማስተኛት ያውቁበታልና። ደብረ ታቦር የስልጣኔ ጮራ የታየባት፣ ንጉሡና ባለሟሎቹ የወደዷት፣ ታሪክ ያከበራት፣ ሃይማኖት የጠበቃት፣ ጀግንነት የከለላት የደጋጎች እና የጀግኖች ከተማ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አጅባር:- ምስጢር የተገለጠበት፤ ንጉሥ የሠረገበት”
Next articleዓመት ሙሉ አምራች የኾነውን የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ሰላም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መኾናቸውን የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር የጸጥታ አካላት ገለጹ።