“አጅባር:- ምስጢር የተገለጠበት፤ ንጉሥ የሠረገበት”

57

ባሕር ዳር: ጥር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሊቃውንቱ ጉባኤያትን አደረጉበት፣ ስለ ሃይማኖት መከሩበት፣ ምስጢር ገለጡበት፣ የረቀቀውን ጥበብ በፈጣሪ እየተመሩ ነገሩበት፣ የከበደውን አቀለሉበት፣ ያልተፈታውን ፈቱበት፣ የደነደነውን ልብ በጥበባቸው አለዘቡበት።

ንጉሠ ነገሥቱ ሠርግ ሠረጉበት፤ የጠፋች ደስታቸውን መለሱበት። መኳንንቱን፣ መሳፍንቱን፣ ሊቃውንቱን፣ የጦር አበጋዞቻቸውን፣ የእልፍኝ አስከልካዮቻቸውን፣ በፊታቸው፣ በኋላቸው፣ በግራ እና በቀኛቸው እጅ እየነሱ የሚከቧቸውን ባለሟሎቻቸውን ጠርተው ዓለም አዩበት፣ የንጉሥ ሙሽራ ታየበት፣ ዘውድ እና ሠርግ ተገናኘበት።

ዘውድ የጫኑ ንጉሥ ከንግሥና ሙሽራ በላይ ሌላ ሙሽርነት ጨመሩበት፣ በሚያስፈራው ግርማቸው ተገማሸሩበት፣ በሚያስደነግጠው ክብራቸው ታዩበት። በዚያ ሥፍራ እጥፍ ድርብ ግርማ ተደራረበበት፣ እልልታና ምስጋና በዛበት፣ ፉከራና ሽለላ በረከተበት። ንጉሡ ሠርግ ሠርገዋል፣ ተሞሽረዋልና ያ ሥፍራ ደስታ መላበት። ሆታው አየለበት።

አንዳንድ ሥፍራዎች አሉ ከሁሉ የሚመረጡ፣ በከበረ ታሪክ ላይ የሚቀመጡ፣ ታሪካቸውን ትውልድ ሲሰማቸው ለነብስ የሚጣፍጡ፣ ትውልድ የሚኮራባቸው፣ እውነት የሚገለጥባቸው፣ ጥበብ የሚፈስስባቸው፣ ከዘመን ዘመን የማይቋረጥ ታሪክ የሚሠራባቸው፣ ታሪክም የሚነገርባቸው።

ዘመናት አልፈው ዘመናት ሲተኩ የትናንት ታሪክ እየተነገረበት፣ የዛሬ ታሪክ እየተሠራበት፣ ለነገ ታሪክ እየተመከረበት፣ እየተዘከረበት፣ ሥርዓት እየጸናበት፣ ሃይማኖት እየተሰበከበት፣ እሴት እየተገለጠበት፣ ጀግንነት እየታየበት፣ የአባት እና የእናት ቃል ኪዳን እየተጠበቀበት፣ ልጅ የአባቱን አደራ እየተቀበለበት፣ ቃሉን ላይሽር ቃሉን እየሠጠበት ዛሬ ላይ ደርሷል። ስሙ በግርማ ይነሳል፣ በኩራት ይወሳል አጅባር።

አጅባር ሜዳ ብቻ አይደለም ፈረሶች የሚግጡበት፣ በቅሎዎች የሚውሉበት፣ ልጆች የሚጫወቱበት፣ እንቦሶች የሚፈረጥጡበት፣ ላም እና በሬዎች ፣ ወይፈን እና ጊደሮች የሚሠማሩበት፣ እረኞች ዋሽንት የሚነፉበት።

እጅባር ብራና ነው ታሪክ የሚነበብበት፣ ቀለም ነው ታሪክ የሚፃፍበት፣ መንበር ነው ታቦታት የሚቀመጡበት፣ ቤተመቅደስ ነው ኪዳን የሚደረስበት፣ ቅዳሴ የሚቀደስበት፣ ስጋና ደሙ የሚፈተትበት፣ ሕዝብ ሁሉ የሚሠባሠብበት፣ በረከትና ረድኤት የሚቀበልበት፣ አጅባር ዙፋን ነው ነገሥታት የሚቀመጡበት፣ እልፍኝ ነው ግብር የሚበላበት፣ አዳራሽ ነው ስለ ሀገር አንድነት የሚመከርበት፣ ስለ ሀገር ፍቅር የሚዘከርበት። ቃል ኪዳን ነው የሀገር ፍቅር የሚጸናበት። ከሜዳ በላይ እልፍ ነገር የተሠራበት ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ልዑላን ደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት መምህር መምህረ መምህራን የኔታ በጽሐ ዓለሙ ነገረ ሃይማኖት፣ ነገረ ቤተ ክርስቲያን እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በጉባኤያት ይወሰናሉ ይላሉ። ሊቃውንቱ በተለያዩ ጊዜያት ጉባኤያትን አድርገዋል። ጉባኤ ኒቅያ አርዮስ የተረታበት፣ አፈ ጉባኤው ለእለስክንድሮስ የነበረበት፣ በቁስጥንጥንያ የተደረገው መቅዶንዮስ የተረታበት፣ ሊቁ ጢሞቲዎስ ድል የነሳበት፣ በኤፌሶን የተካሄደው ንስጥሮስ የተወገዘበት፣ አፈጉባኤው ቅዱስ ቄርሎስ የነበረበት ጉባኤያት በታሪክ ከፍ ብለው ይነሳሉ ይሏቸዋል።

አባ ጎርጎርዮስ የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በሚለው መጽሐፋቸው ከጉባኤ ኒቅያ፣ ከጉባኤ ቁስጥንጥንያ እና ከጉባኤ ኦፌሶን በተጨማሪ ጉባኤ ኬልቄዶን መካሄዱን ጽፈዋል። አባ ጎርጎርዮስ በመጽሐፋቸው እንደ እህቶቿ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የኬልቄዶንን ጉባኤ ውሳኔ እና ቀኖና አልተቀበለችውም። አትቀበለውም ብለው አስፍረዋል።

ሊቃውንቱ ይሰባሰባሉ፣ ጉባኤያትንም ያደርጋሉ፣ በአንድ ሃይማኖት በተመሳሳይ አስተምህሮ ይጸናሉ። ከአስተምህሮው የወጣውንም በትክክለኛው አስተምህሮ ያሳምናሉ። ድልም ይነሳሉ። ሥርዓት አፈርሳለሁ፣ ሕግም እጥሳለሁ ያለውን አውግዘው ይለያሉ። በዓለም ታሪክ በሃይማኖት ላይ የተለየ አስተምህሮ የያዙ፣ አስመስለው የመጡ ሰዎች በተነሱ ጊዜ ጉባኤያት ይደረጋሉ። በጉባኤያትም ትክክለኛው አስተምህሮ ይነገራል። ይገለጣል ነው የሚሉት።

ሊቁ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የተለያዩ ዘመናት ጉባኤያት ተካሂደዋል። በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአክሱም ጽዮን ታላቅ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር። ጉባኤውም እንደ ንቅያ ሁሉ 318 ሊቃውንት ተሠብሥበው ነበር። በታሠበው ልክ በነገረ ሠሪ ጉባኤው ባይሰምርም፡፡

በዘርዓያቆም ዘመንም ሊቃውንቱ ጉባኤያትን አካሂደው ነበር። ይሄ ብቻ ጉባኤ አልነበረም ሌሎች ጉባኤያትም በየዘመናቱ ተደርገዋል። በመናገሻዋ በጎንደር በርከት ያሉ ጉባኤያት ተካሂደዋል። በነገሥታቱ ዘመን በተለይም በአጼ ፋሲል ዘመነ መንግሥት በካቶሊካውያን እና በተዋሕዶ ሃይማኖት ሜንዲዝ እና በትረ ጊዮርጊስ ያደረጉት ጉባኤ ይጠቀሳል።

ይህም ጉባኤ በታሪክ ተመዝግቦ ያለ ከፍ ያለ ጉባኤ ነበር። በአጼ ዮሐንስ (በፃዲቁ ዮሐንስ) ዘመንም በቅባት፣ በተዋሕዶ እና በጸጋ ሃይማኖት መካከል በተፈጠረው ችግርም ጉባኤ ተካሂዶ ነበር ይላሉ ሊቁ። ፃዲቁ እየተባሉ የሚጠሩት አጼ ዮሐንስም በጉባዔው ላይ ተቀምጠው ነበር። በዚህም ጉባኤ የተዋሕዶ ሊቃውንት ድል አድርገው በንጉሡ አዛዥነት አዋጅ ተነገረ። በአጼ ዳዊትም በጎንደር አዘዙ ተክለሃይማኖት ጉባኤ ተደርጎ እንደነበር ሊቁ ያነሳሉ። የተዋሕዶ ሃይማኖት ሊቃውንትም ድል አደረጉ። በደስታም ከአዘዞ እስከ አጣጣሚ ሚካኤል ድረስ በደስታ ሄዱ።

በአጼ በካፋ ዘመንም ከግብፃውያን ሊቃውንት ጋር ጉባኤ ተደርጎ ነበር ይላሉ ሊቁ። በዚያን ዘመን የነበሩ አቃቢ እሳት ከብቴ የተባሉ ሰው አፈጉባኤ ኾነው ጉባኤው ተካሄደ። አቃቢ እሳት ከብቴም ድል አደረጉ። በኋለኛው ዘመንም አጼ ቴዎድሮስ በእናታቸው እንጂ በአባታቸው ከቤተ መንግሥት የሚመዘዝ ሀረግ የላቸውምና ንግሥና አይገባቸውም የሚል ጉዳይ በተነሳ ጊዜ ጉባኤ ተደርጎ ነበር። በዚህም ጉባኤ የቴዎድሮስን ንግሥና የሚያጸና መልስ ተገኘ። ሊቃውንቱ በንግሥናቸው ተስማሙ።

ጉባኤያት እየቀጠሉ የደብረ ታቦር አጅባር ሜዳ ጉባኤ ዘመን ደረሰ። ይህም ጉባኤ በዘመነ ቴዎድሮስ የተካሄደ ነበር። ጉባኤውን የጠሩት አጼ ቴዎድሮስ ነበሩ። በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ሊቃውንትም ተሠባሠቡ። ሊቁ ሲናገሩ አጼ ቴዎድሮስ ጉባኤውን የጠሩበት ምክንያት የመጀመሪያው የሀገር ፍቅር ነው ይላሉ። ሁለተኛውም የሃይማኖት ፍቅር ነው። አጼ ቴዎድሮስ ስለ ምን ይሄን ጉባኤያት አስጠሩት የተባሉ እንደሆነ ከእርሳቸው በፊት በነበረው በዘመነ መሳፍንት የሃይማኖት ሽኩቻ ነበር። እርሳቸውም ይሄን የሃይማኖት ሽኩቻ ይዘጉ ዘንድ ጉባዔውን አስጠሩ።

አጼ ቴዎድሮስም በጉባኤው ሀገሬን እመራ ዘንድ አምላክ ቀብቶኛል። ሀገሬ አንድ ኾና እንድትቀጥል የሊቃውንቱ ምክር ያስፈልገኛል። የሊቃውንቱን ምክር በውል ለማግኘት ደግሞ አንድነታችሁ ያስፈልገኛል። ስለዚህም ተነጋግራችሁ አንዲት እውነተኛ ሃይማኖት እንድትይዙና እኔንም ልጃችሁን እንድትመክሩኝ እፈልጋለሁ። በመካከላችሁ ጠብ እና ጭቅጭ ሳይኖር ተመካክራችሁ አንዲት እውነት አውጥታችሁ በእናንተ እየተመከርኩ ሀገሬን መምራት እፈልጋለሁ ሲሉ በትሕትና ጠየቋቸው ይላሉ ሊቁ።

በዚህም ጊዜ አንድ ሊቅ “አጼ ቴዎድሮስ ቸርነታቸውን ቆራጥነታቸው፣ ቆራጥነታቸውን ቸርነታቸው ሳይጣሉባቸው የሚኖሩ ንጉሥ ናቸው” አሉ ይባላል። መፃሕፍት ተመረመሩ። ሊቃውንቱ ምስጢሩን አመሰጤሩ። ሊቃውንቱም ተስማሙ። መምህረ መምህራን የኔታ በጽሐ የአጅባር ሜዳ ጉባኤ የታሪክ ሰዎች ያልተረባረቡበት ጉባኤ ነው ይሉታል። በአጅባር የተካሄደው ጉባኤ የራሱ ጠባይ የነበረው ነው ይላሉ። በሌሎች ጉባኤያት አንዱ ረቶ ሌላኛው ተረትቶ የሚሄድበት ነበር። በዚህ ጉባኤ ግን ሁሉም ተስማምተው በአንድ ሃይማኖት አምነው የተለያዩበት ነበር ይላሉ። በዚህም ጉባኤ ሊቃውንቱ በደስታ ቅኔ ሲቀኙ ዋሉ ይላሉ ሊቁ።

አራት ዓይና ጉሹ የተባሉ ሊቅም ከሁሉ የላቀ ቅኔ ተቀኙ አሉ ” ሁለቱ ወንድማማቾች አጼ ቴዎድሮስ እና አቡነ ሰላማ ባሉበት ተደርጎ የማያውቅ ነገር ተደረገ። ለነፍሱ ሥራ ጥበበኛ የኾነ ቴዎድሮስ ጽዮንን ማደሪያው አድርጓታልና የማይደረግ ነገር ተደረገ። በታቦር ጉባኤውን ባደረገ ጊዜ የማይደረግ ነገር ተደረገ። ይሄ ጉባኤ ከተደረገማ ከዚህ በኋላ ቁስጥንጥንያ ምንድን ናት፣ ከዚህ በኋላ ቁስጥንጥንያ ማለት ኢትዮጵያ ናት። ንቂያም ደብረ ታቦር ናት” አሉ ይላሉ ሊቁ። ንቅያን፣ ኤፌሶንን እና ቁስጥንጥንያን ከመተረክ ይልቅ ደብረ ታቦርን እና አጅባርን እንዲተርኩ ያስተላለፉት ቅኔ ነበር ይባላል።

አጅባርም ጉባኤ እንዲኾን የተደረገበት ምክንያት የንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ መናገሻ በደብረ ታቦር መኾኑ፣ የጳጳሱም መቀመጫ በዚያው ስለነበር፣ ጉባኤውን የጠሩ ንጉሡ ስለኾኑ እና የሜዳው ሥፋትም ታላቅ በመኾኑ ነው ይላሉ ሊቁ። አጅባር ከዚያ አስቀድሞም የታቦታት ማደሪያ እንደነበር ይናገራሉ። አጅባር ጉባኤ ተደርጎበታል። ሃይማኖት ጸንቶበታል ነው የሚሉት።

ሊቁ ለመኾኑ አጅባር ማለት ምን ማለት ይኾን? ሲባሉ ሀጅ ባሕር ማለት ነው። በስፍራው ባሕር ነበር። ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ተተክሎ ታቦተ ሕጉ ወጥቶ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ባሕሩ ያስቸግር ነበር። በዚያም ጊዜ ሊቃውንቱ በሐሩን ብናስተነፍሰው እኮ ይሄዳል። ጥምቀቱንም በዚህ እናክብር አሉ ይባላል። ስያሜውንም ከዚያው አገኘ የሚሄድ ባሕር እንደማለት ነው ይላሉ።

ሊቁ የአጅባርን ጉባኤ የሀገር ፍቅር የወለደው ጉባኤ ይሉታል። የሀገርን አንድነት የሚወዱ ነገሥታት የሊቃውንቱን አንድነት፣ የሊቃውንቱን ኅብረት ይፈልጋሉ። አጼ ቴዎድሮስም የሀገር ፍቅር ነበራቸውና ሊቃውንቱ አንድ ይኾኑ ዘንድ ወደዱ። የወደዱትንም አደረጉ።

እነሆ ዛሬም አጅባር ታላላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እየተፈጸሙበት ቀጥሏል። ይህ ታሪካዊ ሜዳ አጼ ሠይፈአርድ ደብረ ታቦር ኢየሱስን አስተክለው ጥምቀተ ባሕሩን አጅባር ሜዳ እንዲኾን ካደረጉ ጊዜ ጀምሮ በታሪካዊቷ ከተማ የተተከሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ጥምቀተ ባሕራቸውን በአጅባር አድርገዋል ይላሉ ሊቁ። ስለ ምን ቢሉ ታሪካዊ ነውና። በአጅባር ከሌሎቹ ሁሉ በተለየ መልኩ ረዘም ላሉ ቀናት ታቦታት እየወረዱ ጥምቀት ይከበራል። ሕዝቡና ምድሩም ይባረካል። ሊቁ ሲናገሩ አጅባር የታቦታት ሁለተኛ መንበራቸው ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ሕዝብ እንዳሁኑ ሳይሰፋ በጥምቀት ጊዜ የአጼ ቴዎድሮስ ድንኳን ይዘረጋ ነበር።

አጅባር የንጉሥ ዳስ የተጣለበት፣ የንጉሥ ሰርግ የተሰረገበት ነውም ይላሉ ሊቁ። አጼ ቴዎድሮስ በታወሱ ጊዜ አብሮ የሚወሳ ታላቅ ሜዳም ነው። አጅባር ነገሥታቱ፣ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ የፈረስ ጉግስ የሚጋልቡበት፣ ልዑላኑ የፈረስ ጉግስ የሚማሩበት፣ የቤተ መንግሥቱን ትምህርት እና የጦሩን ስልት የሚያውቁበት ነው። የትናንት ታሪክ ሀገርን ከፍ ያደርጋል፣ የታላቋን የኢትዮጵያን ታሪክ ማውጣት ይገባል፣ የአባቶች ታሪክ ድንቅና ረቂቅ ነውና። ሊቁ እንደሚሉት ኢትዮጵያ በተጠራች ጊዜ የዓለም ልብ የሚደነግጠው አባቶች በሠሩት ታሪክ ነው። ይህን የከበረ ታሪክ ለዓለም ማስተዋወቅ ግድ ይላል፣ አጼ ቴዎድሮስን የሚወድ እና እሳቸውን የሚያነሳ ሁሉ አጅባርን ያንሳው ነው የሚሉት።

አጅባር ላይ የተካሄደው ጉባኤ በታሪክ እየተዘከረ እና እየተነገረ ይኖር ዘንድ ከሊቃውንቱ ጉባኤያትን ማሳደግ ይጠበቃል ይላሉ። የከበረው ታሪክ ይወጣ እና ይገለጥ ዘንድ ግድ ይላልና። አጅባር የታላቅ ታሪክ ባለቤት ታላቅ ምድር። ሂዱ ታሪክ በበዛበት፣ ሃይማኖት በጸናበት፣ ሊቃውንቱ በማይነጥፉበት፣ ሕዝብ በሚሠባሠብበት፣ ታቦታት በሚያድሩበት፣ ጀግኖች በሚመላለሱበት፣ ነገሥታት በተመላለሱበት በአጅባር ሰማይ ሥር ተጠለሉ። ያን ጊዜ በአንድ ሜዳ እልፍ ነገር ታገኛላችሁ።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ለስድስት ወራት የታወጀው አስቸኳይ አዋጅ ለአራት ወራት ተራዘመ።
Next articleደብረ ታቦር ጎዳናዎቿን አስውባ፤ እልፍኞቿንም አሳምራ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው።