የአካባቢያቸውን ጸጥታ የማረጋገጥ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ የደጀን ዙሪያ እና የደጀን ከተማ አሥተዳደር ሠልጣኝ የጸጥታ አካላት ገለጹ።

16

ባሕር ዳር: ጥር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የዜጎች ሰላም እንዲጠበቅ እና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የጸጥታ አካላት የአመለካከት እና የክህሎት ሥልጠና በደጀን ከተማ አሥተዳደር እየተሰጠ ይገኛል። ሥልጠናው የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ እና ልማት እንዲቀጥል ለማስቻል ዓላማው ያደረገ ነው።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሐኑ በክልሉ የነበረውን ቀውስ በመቀልበስ የተዛባ አመለካከት ይዘው ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ አካላት የሰላም ጥሪ ስለመደረጉ ተናግረዋል፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ዋና አሥተዳዳሪው ሥልጠናው የተደራጀ፣ የተጠናከረ እና በሥነ ምግባር የታነጸ የጸጥታ አካል በማዋቀር የሕዝብን ደኅንነት የማረጋገጥ እና ሀገር የማስቀጠል ኀላፊነት የሚሰጥ መኾኑን ለሠልጣኞች አስረድተዋል። የጸጥታ አካላት የተሠጣቸውን ተልዕኮ ማሳካት እና መፈጸም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ የ403ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ሙላው በየነ አውቀውትም ኾነ ሳያውቁት በተሳሳተ መንገድ የተሠለፉ አካላት በሰላም ወደ ቤተሠባቸው እንዲመለሱም መክረዋል።

የሕግ ማስከበር ኀላፊነትን ከአካባቢው የጸጥታ ኀይል ጋር ተባብሮ መሥራት ላይ የሚሠራው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለጹት። ሥልጠናውን እየተከታተሉ የሚገኙ የጸጥታ አካላትም የእርስ በርስ መተማመንን እና አንድነታቸውን አጎልብተው የአካባቢያቸውን ጸጥታ የማረጋገጥ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡- የኔነህ ዓለሙ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዘንድሮው የመርቆሪዎስ በዓልና የፈረስ ጉግስ ከወትሮዉ በተለየ በዓድዋ ንግስቷ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የመታሰቢያ ሐውልትና አደባባይ ምርቃት ታጅቦ በድምቀት ይከበራል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)
Next articleየሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ለስድስት ወራት የታወጀው አስቸኳይ አዋጅ ለአራት ወራት ተራዘመ።