“የዘንድሮው የመርቆሪዎስ በዓልና የፈረስ ጉግስ ከወትሮዉ በተለየ በዓድዋ ንግስቷ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የመታሰቢያ ሐውልትና አደባባይ ምርቃት ታጅቦ በድምቀት ይከበራል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)

40

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በደብረታቦር ከተማ ነገ የሚከበረውን የመርቆሪዎስ በዓል አስመልክቶ ያስተላለፉት መልእክት።

በአማራ ክልል ከሚከበሩ ደማቅ በዓላት መካከል አንዱ የጥንተ ታሪክ ባለቤት በሆነችዉ በደብረታቦር ከተማ ጥር 25 የሚከበረዉ የመርቆሪዎስ በዓል ነዉ። በዕለተ መርቆሪዎስ የፈረስ ጉግስ ጨዋታ ፍልሚያና ሌሎች ባህላዊ ጨዋታዎች ደምቀው ይውላሉ።

የደብረታቦር የፈረስ ጉግስ ከ18ኛው ክፍለዘመን ቀደም ብሎ በደብረታቦር ሲከበር ቆይቶ በመሃል ተቋርጦ የራስ ጉግሳ ባለሟል በነበሩት ፊታውራሪ አለነ በተባሉ ግለሰብ በድምቀት መከበር እንደጀመረ ይነገራል። የፈረስ ጉግስ ጨዋታ ንጉሶች የሚወዱት ባህላዊ ጨዋታ በመሆኑ በአካል በመገኘት ይታደሙት እንደነበር ታሪክ ይናገራል።

ከዓድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ ባሉት ጊዚያት የፈረስ ጉግስ በደብረታቦር እንደ መዝናኛ ተወዳጅ ጨዋታ እንደነበርና በኋላም በዓድዋ ጦርነት ወቅት በርካታ የበጌምድር ጦረኞች ሲዘምቱ ፈረሰኞቹ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው ታሪክ ያወሳል። የፈረስ ጉግስ በደብረታቦር ሲከበር በአንድ በኩል ከሃይማኖታዊ የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሪዎስ ፈረሰኛ ገድሉን ለመዘከር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞ ጠላት ከዉጭ በመጣ ጊዜ ለሀገር ዳር ድንበር በፈረስ የሚዘምቱትን፤ በሰላሙ ጊዜ በፈረስ ጉግስ ጨዋታ የሚደምቁበትን ጊዜ ለማስታወስ በብዙ ባህልና እምነት ደምቆ የሚከበር በዓል ነው።

በዚህ በዓል እምነት፣ ባህል፣ ወግና ልምድ ባንድ ላይ ተደምረዉ አሸብርቀዉና ደምቀው በተንጣለለው የአጅባር ሜዳ የቅዱስ መርቆሪዎስ በዓልና የፈረስ ጉግስ ትርኢት ምዕመኑን እና የበዓሉ ታዳሚዎችን ያስደምማሉ። የመርቆሪዎስ ንግስ እና የፈረስ ጉግስ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ኪነ ጥበባዊ ክዋኔዎችን አካቶ በድምቀት ይከበርበታል።

በዕለቱ ድንቅና ቄንጠኛ ፈረሰኞች በአጅባር ይገማሸራሉ፤ በጉግስ ፍልሚያ ያደርጋሉ የጀግኖች አርበኞች የአርበኝነት ታሪክ ይታወስበታል። በዓሉ ለከተማውና ለአካባቢው ብሎም ለክልላችንና ለሀገራችን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ሁኖም በሰፊው እንድንሰራበት የሚያነቃቃና በጎ ጅምሮች የታዩበትም ነው።

የዘንድሮው የመርቆሪዎስ በዓልና የፈረስ ጉግስ ከወትሮዉ ለየት የሚያደርገው የዓድዋ ንግስቷ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የመታሰቢያ ሀውልትና አደባባይ ምርቃት በዚሁ እለት የሚካሄድ መሆኑ ነው። የምረቃ ሥነስርዓቱ ከፌዴራልና ከክልል የሚመጡ በርካታ እንግዶች፣ አርቲስቶችና ሌሎችም ተሳታፊዎች በተገኙበት ይካሄዳል።

ሰላም ወዳዱ የደብረታቦር እና አካባቢዉ ሕዝብም ከተላያዩ የሀገሪቱ ክፍል በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅቱን ጨርሷል። በመሆኑም ጥር 25 በዉቢቷ ደብረታቦር ከተማ በመገኘት በመርቆሪዎስ በዓል ላይ እንዲሳተፉ እና የፈረስ ጉግስ ጨዋታውን እንዲታደሙ ጥሪየን አስተላልፋለሁ።

Previous articleየሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኛነት እንደሚሠሩ የጠገዴ ወረዳ የጸጥታ አባላት ተናገሩ።
Next articleየአካባቢያቸውን ጸጥታ የማረጋገጥ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ የደጀን ዙሪያ እና የደጀን ከተማ አሥተዳደር ሠልጣኝ የጸጥታ አካላት ገለጹ።