የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኛነት እንደሚሠሩ የጠገዴ ወረዳ የጸጥታ አባላት ተናገሩ።

12

ሁመራ: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኛነት እንደሚሠሩ የጠገዴ ወረዳ የጸጥታ አባላት ተናግረዋል። “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልእክት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ለጸጥታ አመራሮች እና አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

በዞኑ በአራት ወረዳ እና በአምስት ከተማ አሥተዳደሮች ለጸጥታ አካላት እየተሰጠ የሚገኘው ሥልጠና የሠልጣኞችን አቅም የሚገነባ እና ሙያዊ ግዴታን ለመወጣት የሚያግዝ ነው ተብሏል።

በጠገዴ ወረዳ ማክሰኞ ገቢያ የሥልጠና ማዕከል የተገኙት የጠገዴ ወረዳ አሥተዳዳሪ ጌታሁን ብርሃኔ ሥልጠናው በወረዳ፣ በዞን እና በክልል ደረጃ እየተፈጠሩ ያሉ የጸጥታ ችግሮችን በመቅረፍ የአካባቢን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በወረዳው የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን ከምንጩ ለማስቀረት እና ኅብረተሰቡ ከቦታ ቦታ በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ሥልጠናው ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት።

በወረዳው ብሎም በዞኑ እየተካሄደ የሚገኘው መጠነ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረው የጸጥታ አካላቱ ከሥልጠናው በሚያገኙት ልምድ ይበልጥ የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያግዝ እና መነሳሳት የሚፈጥር እንደኾነም አንስተዋል።

ሠልጣኞች በሥልጠናው ሰላምን የሚያረጋግጡበት ሙያዊ ሥነ ምግባርን ተላብሰው ሕዝብን በቅንነት እና በእኩልነት የሚያገለግሉበትን ልምድ የሚቀስሙበት ነው ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ እንዲሁም የጠገዴ ወረዳ ማሠልጠኛ ማዕከል አስተባባሪ ሙሐመድኑር ሲራጅ የዞኑ የጸጥታ አካላት የአካባቢን ሰላም ለማስጠበቅ ያላቸው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መኾኑን አንስተዋል።

ሥልጠናው የጸጥታ አካላትን አቅም የሚያሳድግ ሙያዊ ዕውቀትንም እንዲያዳብሩ የሚያግዝ በመኾኑ ሠልጣኞች በትኩረት ሊከታተሉ እንደሚገባ አንስተዋል።

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚተጉ አንስተው ከሥልጠናው በቂ እውቀት እና ልምድን ለመቅሰም ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል። የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኛነት እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል። ለዞኑ ሕዝብ አስተማማኝ የሰላም በር ለመኾን በትጋት እንሠራለን ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተለያዩ ሙያና ኀላፊነቶች ሕዝብን እና ሀገርን በቅንነት በማገልገል የሚታወቁት አቶ መስፍን አበረ ይማም ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ።
Next article“የዘንድሮው የመርቆሪዎስ በዓልና የፈረስ ጉግስ ከወትሮዉ በተለየ በዓድዋ ንግስቷ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የመታሰቢያ ሐውልትና አደባባይ ምርቃት ታጅቦ በድምቀት ይከበራል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)