በተለያዩ ሙያና ኀላፊነቶች ሕዝብን እና ሀገርን በቅንነት በማገልገል የሚታወቁት አቶ መስፍን አበረ ይማም ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ።

22

ባሕር ዳር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ መስፍን አበረ ይማም በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግሥት በቀድሞው አጠራር ባሕር ዳር አውራጃን ወክለው በሕዝብ እንደራሴነት ተመርጠው እስከ ሥርዓቱ ማብቂያ ሕዝብን አገልግለዋል።

በ1965 ዓ.ም ያገኙት ይህ እድል በሕዝብ ዘንድ ለነበራቸው ተቀባይነት እና ታማኝነት ትልቅ ማሳያ መኾኑን ጓደኞቻቸው እና የሥራ አጋሮቻቸው ለአሚኮ ገልጸዋል። በንጉሡ ዘመን በወጣትነታቸው ሕዝብን ወክለው በእንደራሴነት ያገለገሉት አቶ መስፍን በደረግ ጊዜም በተለያዩ አካባቢዎች አሥተዳዳሪ ኾነው በቅን አገልጋይነት ስለ መሥራታቸው በሕይወት ታሪካቸው ተነስቷል።

በሜጫ፣ በሞጣ፣ በቆላ ደጋ ዳሞት፣ በባሕር ዳር እና መተከል አውራጃ አሥተዳዳሪ ኾነው ባገለገሉባቸው ጊዜያትም በአገልጋይነት እና ቅንነታቸው በሕዝብ የተወደዱ ነበርም ተብሏል።
ሀገር ወዳድና ተቆርቋሪ የነበሩት አቶ መስፍን ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ የሚመሩትን ሕዝብ በማስተባበር እና በማነሳሳት የሀገር ዳር ድንበር እንዳይደፈር ትልቅ ሥራ መሥራታቸውን ጓደኞቻቸው ገልጸዋል።

ከመንግሥት ኀላፊነታቸው በተጨማሪ በመምህርነት ሙያቸው በአስተማሪነት እና በርእሰ መምህርነት በርካቶችን ቀርጸው ለቁምነገር አብቅተዋል። አቶ መስፍን አበረ ይማም ከእናታቸው ወይዘሮ አጸደወይን ዘለቀ፣ ከአባታቸው አርበኛ ደጅአዝማች አበረ ይማም በድሮዉ ጎጃም ጠቅላይ ግዛት በባሕርዳር አዉራጃ ሜጫ ወረዳ ቅርቃኛ ሚካኤል ቀበሌ ሐምሌ 3 ቀን 1934 ዓ.ም እንደተወለዱ የሕይወት ታሪካቸው ያትታል።

አባታቸው አርበኛ አበረ ይማም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት የአምስት ዓመቱ ጦረነት ትልቅ ጀብድ የፈጸሙ እና በአርበኝነታቸው አንቱ የተሰኙ እንደነበሩም ተገልጿል። አቶ መስፍን እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትምህርት አሥተዳደር ዘርፍ በዲፕሎማ በኃላም የ2ኛ ዲግሪያቸውን በማኔጅመንት ማግኘታቸው በሕይወት ታሪካቸው ላይ ተነስቷል። አቶ መስፍን አበረ የጡረታ ጊዜያቸውን በተለያዩ የማኅበራዊ ሥራዎች የሳልፉ አንደነበር ከጓደኞቻቸው መረዳት ተችሏል።

ሀገራቸውን በታማኝነት ያገለገሉት፣ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እና ተወዳጅነት የነበራቸው አቶ መስፍን አበረ ይማም ባደረባቸው ህመም በሀገር ውስጥ እና በውጭ በህክምና ሲረዱ ቆይተዋል።ነገር ግን ሳይሻላቸው ቀርቶ በተወለዱ በ82 ዓመታቸው ጥር 18 ቀን 2016 ዓ.ም አርፈዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም በባሕርዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም ጥር 23/2016 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኘበት ተፈጽሟል።

ዘጋቢ:- አስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleትምህርት ሚኒስቴር ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ያስገነባው የጸመራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።
Next articleየሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኛነት እንደሚሠሩ የጠገዴ ወረዳ የጸጥታ አባላት ተናገሩ።