
ሰቆጣ: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜኑ ጦርነት ወድሞ የነበረው የሰቆጣ ዙርያ ወረዳ ጸመራ 1ኛ ደረጃ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ትምህርት ሚኒስቴር አስገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት አድርጎታል።
ትምህርት ቤቱን መርቀው የከፈቱት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ “በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በመልሶ ግንባታ ትምህርት ሚኒስቴር ገንብቶ ስላስረከበ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ስም አመሥግነዋል።
የጸመራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጣፈጠ ወልዱ “መንግሥት ይህንን የመሰለ ግንባታ ሲሠራልን እኛም ልጆቻችን በእውቀት እንዲገነቡ በማድረግ ለማስተማር ዝግጁ ነን” ብለዋል። ከኅብረተሰቡ የሚጠበቀውን የአጥር ሥራ ለመሥራትም ዝግጁ እንደኾኑ ተናግረዋል።
ተማሪ ወይንሸት በላይ እና ተማሪ ጌታሁን አስማረ የተሠራላቸው ዘመናዊ የመማርያ ክፍል የመማር ፍላጎታቸውን ከፍ እንዳደረገው ተናግረዋል። የሰቆጣ ዙርያ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌትነት እሸቱ የጸመራ ትምህርት ቤት በወረዳው ካሉ አንጋፋ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ሲኾን ነባርነቱን የሚመጥን ሕንጻ በመገንባቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ትምህርት ቤቱ ሦስት ሕንጻ ያለው ሲኾን 10 የመማርያ ክፍሎች እና ሁለት ዘመናዊ የመጸዳጃ ቤቶችንም ያካተተ እንደኾነ ጠቁመዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰይፋ ሞገስ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አምስት ትምህርት ቤቶችን ትምህርት ሚኒስቴር እያስገነባ እንደኾነ አስታውሰዋል፡፡ በቀጣይም አስፈላጊውን ግብዓት ለማሟላት ስለመዘጋጀታቸው ነው ያስረዱት።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከአሁን በፊት በትምህርት ሚኒስቴር የተገነቡት ዛሮታ ትምህርት ቤት እና ዘናልቃ ትምህርት ቤት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸው የሚታወስ ነው።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!