በተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ሥራ የደን ሽፋን መጨመሩን የደቡብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።

28

ባሕር ዳር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ በተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ የደን ሽፋኑን መጨመሩ መቻሉን የደቡብ ጎንደር ዞን አስታውቋል። “ተሳትፏዊ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ለምርት እድገትና ለዘላቂ የኅብረተሰብ ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ የተቀናጀ የተፋሰስ ንቅናቄ ተካሂዷል።

የፋርጣ ወረዳ ሰሃርና ቀስናጥ ቀበሌ ነዋሪው የማታው ቢሰጥ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ለዓመታት ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ለረጅም ዓመታት የታረሱ እና የተቦረቦሩ መሬቶችን ለምነታቸውን በመመለስ ምርታቸውን ማሳደጋቸውንም አስታውቀዋል። አርሶ አደሮች አሁን ላይ በራሳቸው ተነሳሽነት የተፈጥሮ ሀብት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ምርትን ከማሳደግ ባለፈ የንፁሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በተፈጥሮ ሀብት ሥራ የፍራፍሬ ምርት እያደገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በፋርጣ ወረዳ የወርቄን ቀበሌ ነዋሪው ይበልጣል ደሴ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ከተጀመረ ጀምሮ አካባቢው ወደ ለምነት እየተቀየረ መሆኑንም ገልጸዋል። የአፈር ለምነት በመመለሱ ምርትም እያደገ መሆኑን ነው የተናገሩት። የተፈጥሮ ሀብት ሥራ አትክልቶች እንዲኖራቸው ማድረጉንም አመላክተዋል። የተፈጥሮ ሀብት ሥራን አጠናክሮ መቀጠል ጥቅሙ ለራስ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፋርጣ ወረዳ ግብርና ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ማዕድነው ብርሃን በወረዳው ላለፉት ዓመታት በተሠራው የተፈጠሮ ሃብት ሥራ የአፈር መከላት መቀነሱንም ገልጸዋል። ተጎድተው የነበሩ አካባቢዎችን በተፈጥሮ ሀብት እየለሙ፣ ማሳዎችም ምርታቸው እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል። በተፋሰስ ልማቱ ንብ በማነብ እና እንስሳት በማድለብ ጥሩ ጥቅም እየተገኘ መሆኑን ነው ያነሱት። የደን ሽፋንም እየጨመረ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ሰላማቸውን እያስጠበቁ የተፈጥሮ ሀብት ሥራቸውን እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አባተ ሽባባው ለዓመታት በተካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ የተራቆቱ አካባቢዎች በልምላሜ እየተሸፈኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል። የተፈጥሮ ሀብት ሥራው የዞኑን የደን ሽፋን ከ4 ነጥብ 8 ወደ 14 ነጥብ 5 በመቶ ማሳደጋቸውንም ተናግረዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ሥራ በለሙ አካባቢዎች ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠራቸውንም አስታውቀዋል። በዘንድሮው ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ለመሥራት እቅድ መያዛቸውንም ገልጸዋል። በዞኑ አብዛኞቹ አካባቢዎች ሰላማቸውን ጠብቀው ወደ ተፈጥሮ ሃብት ሥራቸውን እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ በ2016 በጀት ዓመት በተለያዩ ወረዳዎች የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ይካሄዳል ነው ያሉት። ፋርጣ ወረዳና የተፈጥሮ ሀብት ሥራ የማይነጣጠሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በዞኑ ከአሁን ቀደም በአራት ወረዳዎች የተፈጥሮ ሀብት ሥራ መጀመሩም አስታውሰዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ሥራ የተቀናጀን እና የርብርብ ሥራን እንደሚጠይቅም ተናግረዋል። በአካባቢው ሕዝብን የማይመጥን ያልተገባ ግርግር እንደነበር ያስታወሱት አሥተዳደሪው አካሄዱ የሕዝብን የልማት እና የሰላም ጥማት የማያረካ መሆኑንም ተናግረዋል። በተሠራው ሥራ አንፃራዊ ሰላምን በመመለስ ወደ ልማት ሥራዎች ዞረናልም ብለዋል።

የፋርጣ ወረዳ ነዋሪዎች ሰላማችን ይቅደም ብለው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ማስጀመራቸው የሚደነቅ እንደሆነም ተናግረዋል። ልማታችሁን ለማደናቅፍ የሚመጣ ግለሰብም ሆነ ቡድን እናንተን የሚጠቅም እንዳልሆነ መረዳት አለባችሁም ብለዋል።

በዞኑ በተደረገው የሰላም ጥሪ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች መግባታቸውን ያነሱት ዋና አሥተዳደሪው የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ሥልጠና እየወሰዱ መሆናቸውንም አንሰተዋል። ይሄም ሰላምን በማጽናት ነዋሪዎች ወደ ልማታቸው እንዲገቡ እንደሚያደርጋቸው ነው የተናገሩት። ሰላም በማስጠበቅ ልማትን ማልማት የወቅቱ ዐቢይ ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰላም እጦቱ ይበልጥ ተጎጅ የኾኑት ሴቶች ዘላቂ ሰላም ይሰፍን ዘንድ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡
Next article84ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ በዓል በሰላም መጠናቀቁን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።