
ጎንደር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ “የኢትዮጵያን ሰላም እጠብቃለሁ ምንዳን ለልጆቼ አወርሳለሁ” በሚል መሪ መልእክት የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው። የውይይቱ ተሳታፊዎች ከማእከላዊ ጎንደር ዞን እና ከጎንደር ከተማ የተውጣጡ ሴቶች የተሳተፉበት ሲኾን እየታዩ ያሉ የሰላም እጦቶችን ለመቅረፍ የሴቶች ሚና ጉልህ መኾን እንዳለበት ያለመ ነው።
የምክክሩ ተሳታፊወች አሁን በገጠመው የሰላም እጦት ሴቶች በይበልጥ ተጎጅ እየኾኑ መኾኑን አንስተው ዘላቂ ሰላም ይሰፍን ዘንድም የድርሻቸውን ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት።
በምክክሩ ሴቶች የሰላም ባለቤት ኾነው ሁሉን አቀፍ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ የሰላም እጦት መንስኤ የኾኑ የአመለካከት መዛነፎች እንዲቀረፉ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተነስቷል።
የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል ወይዘሮ አስቴር ከፍታው በሰላም እጦት ይበልጥ ተጎጅ የኾኑ ሴቶች ሀገራዊ መግባባት በመፍጠር ለሰላም መጽናት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማስቻል ይገባል ብለዋል፡፡ ይህን ሚናቸውን እንዲወጡም በተለያዩ አካባቢወች የሚሰጠው የሴቶች ምክክር ቀጣይነት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- ምሥጋናው ከፍያለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!