ሰላማዊ አማራጮችን በመጠቀም ችግርን መፍታት እንደሚገባ የአማራ ሳይንት ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

24

ደሴ: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ኮማንድ ፖስት ከአማራ ሳይንት ወረዳ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አካሂደዋል፡፡ በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በወረዳው ከሰው ሕይወት መጥፋት እስከ ንብረት ውድመት ድረስ ከፍተኛ ቀውስ እንዳስከተለ ነዋሪዎች በምክክሩ አንስተዋል።

በጸጥታ ችግሩ ምክንያት በወረዳው የተጀመሩ ልማቶች ወድመዋል፤ የተጀመሩ ቆመዋል፤ ለወደፊትም ጠባሳ አስቀምጠዋል ሲሉም ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ቦታው ከገባ በኋላ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑንም ነዋሪዎች ጠቅሰዋል፡፡

በጦርነት የሚገኝ ዘላቂ መፍትሔ እንደሌለ የተናገሩት ነዋሪዎች አሁንም ሰላማዊ መፍትሔዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡ እኔ ከሚለው የግለኝነት አስተሳሰብ በመውጣት እና ጉዳዩን ለጸጥታ ኀይሉ ከመተው ባለፈ እንደ ኅብረተሰብ የድርሻን መወጣት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን የተለያዩ የሐሰት ትርክቶች አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ ወደ ውስብስብ ችግር ውስጥ ማስገባቱንም ተናግረዋል፡፡ልዩነትን አቻችሎ በእኩልነት የሚኖርበት ሥርዓት መፍጠር የትውልዱ ኀላፊነት ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ምክክር የሁሉም ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነው ብለዋል፡፡ ከምክክር ውጭ ያለው አካሄድ መፍትሔ አያመጣም ነው ያሉት፡፡

በአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ልዩነት የለም ያሉት አሥተዳዳሪው ጥያቄዎቹ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በምክክር የሚፈቱ መኾናቸውን ነው ያነሱት፡፡ ለዚህም ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡ ልጆቹን መክሮ ወደ ሰላማዊ አማራጭ ማምጣት የማኅበረሰቡ ድርሻ እንደኾነም አቶ አሊ ተናግረዋል

የድርቅ፣ የማዳበሪያ አቅርቦት እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት የጸጥታ ችግሩ እንቅፋት ኾኖ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ ሰላሙ ከተረጋገጠ የውኃ፣ መንገድ እና መሰል ልማቶችን ለማሳለጥ ጥረት እንደሚደረግ ጠቅሰዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እኛ የአገው ሕዝብ ሰላምን ከማንም የማንጠብቅ ሰላማችን በጃችን ያለ በመኾኑ ሰላማችንን የሚያውክ ሁሉ ልክ ወራሪው ጣሊያንን እንደታገልነው ሁሉ የምንታገለው ይኾናል” አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ
Next articleሥልጠናው የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ እና የበለጠ ለመሥራት እንደሚያግዝ የሰቆጣ ዙርያ ወረዳ የጸጥታ አካላት ገለጹ።