
ባሕር ዳር፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር 84ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል በእንጅባራ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡በበዓሉ ላይ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የሰላም አርበኝነት ለወንድማማችነት በሚል መልእክት የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል የአዊን ሕዝብ ከፍታ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የአዊ ሕዝብ ሰላማዊ ሕዝብ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡ ወቅትም ኾነ ዘመናት፣ፖለቲካም ኾነ ፖለቲከኞች ቢቀያየሩም የአዊን ሕዝብ እንደማይቀይር አስረድተዋል፡ የሁኔታዎች አውድ ሲቀያየሩ አሉታዊም ይሁን አወንታዊ ጉዳዮችን የሚረዳ ሕዝብም ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡
ሰላም የሁሉም አጀንዳ ማስፈጸሚያ እንደኾነ በአግባቡ የሚረዳ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ የአገው ሕዝብ ለራሱም ኾነ ለጎረቤቶቹ ሰላምን የሚሰጥ ታላቅ ሕዝብ ነውም ብለዋል፡፡ ለሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚተጋ ሕዝብም እንደኾነ ነው ያስገነዘቡት፡፡ ከአገው ሕዝብ ጋር ግንኙነት ያላቸው ማንኛውም አካላት ግንኙነቱ ለሰላም እና ለወንድማማችነት እንዲኾን እንደሚሹም ገልጸዋል፡፡
“እኛ የአገው ሕዝብ ሰላምን ከማንም የማንጠብቅ ሰላማችን በጃችን ያለ በመኾኑ ሰላማችን የሚያውክ ሁሉ ልክ ወራሪው ጣሊያንን እንደታገልነው ሁሉ የምንታገለው ይኾናል” ብለዋል፡፡ የአገው ሕዝብ አርበኛ የኾነ ሕዝብ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡
የአገው ሕዝብ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን፣ ፍትሃዊ የመንግሥት አሥተዳደርን፣ አዳዲስ የግብርና አሠራርን እና የተለያዩ ማኅበራዊ ሥርዓቶችን በማላመድ ስልጣኔን ለዓለም ያበረከተ ሕዝብ ስለመኾኑም ገልጸዋል፡፡
የአገው ሕዝብ ከተረፈው ብቻ ሳይኾን ከራሱ ላይ ቆርሶ የሚያበላ እና ለሌሎች የሚያስብ ኩሩ እና ደገኛ ሕዝብ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት፡፡ የአገው ሕዝብ በልማቱም በአርበኝነቱም አርዓያ የሚኾን እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
የአገው ሕዝብ አቃፊ እና ደጋፊ የኾነ ሕዝብ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ ለራሱ የሚደረግለትን ለሌላውም የሚያደርግ በሌላ በኩል በራሱ ላይ እንዲኾን የማይፈልገውን በሌላው ላይ እንዲደረግ የማይፈቅድ ኩሩ እና ስልጡን ሕዝብ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት፡፡ ለአብሮነት እንቅፋት የኾኑ ጉዳዮችንም አምርሮ እየታገለ ስለመኾኑም ነው ያስረዱት፡፡
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በኢትዮጵያ በማይዳሰስ ቅርስነት ስለመዝገቡ ገልጸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒሰኮ እንዲመዘገብ ሁሉም እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየውን ሀገርንም ይሁን አካባቢውን የሚረብሽ የጽንፈኝነትን እሳቤ እና ተግባር የአዊ ሕዝብ በአብሮነት እንዲከላከልም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በተሳሳተ እሳቤ ሳይገባቸውም ኾነ ገብቷቸው ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አካላት እየሄዱበት ያለው አካሄድ ጥያቄያቸውን የማይመልስ ከመኾኑም በላይ ለሰባዊ እና ቁሳዊ ጉዳት የሚዳርግ መኾኑን በመገንዘብ ወደ ሰላም እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!