“የሰላም እጦቱ ችግር የሚፈታው ወጣቶች በብሔራዊ አርበኝነት መንፈስን ተላብሰው ለሰላም ሲታገሉ ነው” የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ

14

ባሕር ዳር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ዓድዋ ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ መልእክት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ የአማራ ክልል ወጣቶች የሰላም ጉባኤ ሊያደርጉ መኾናቸውን የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ገልጸዋል።

ጉባኤው የዓድዋን ድል መነሻ በማድረግ የክልሉ ወጣቶች ታሪካቸውን፣ ባሕላቸውን እና እሴቶቻቸውን በመገንዘብ ለዘላቂ ሰላም ብሎም ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

ጉባኤው ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ከጥር 23 እስከ የካቲት 23/2016 ዓ.ም ነው የሚደረገው። የሰላም ጉባኤው ከዓድዋ በዓል ጋር የተያያዘበት ምክንያት የዓድዋ ድል አባቶች እና እናቶች ውስጣዊ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ሀገራቸውን በጠላት ላለማስደፈር ብለው በሕዝባዊ ንቅናቄ የተነሱበት እና ግባቸውንም ያሳኩበት በመኾኑ እንደኾነ አስረድተዋል። በጋራ ያበረ ደግሞ ድል ማስመዝገብ እንደሚቻል እና ለዘመኑ ወጣት ትምህርት እንደሚሰጥ ቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል።

አሁን ሀገሪቱም ይሁን በክልሉ በሰላም እጦት እየተፈተነ ይገኛል ያሉት አቶ እርዚቅ ይህ ውስጣዊ የሰላም እጦት ደግሞ ለውጭ ወራሪ በር የሚከፍት ነው፤ ለድህነትም ያጋልጣል ነው ያሉት፡፡ በመኾኑም ወጣቱ በአንድነት አብሮ በመቆም ድህነትን ማሸነፍ ይገባዋል ብለዋል።

የክልሉ የሰላም እጦት የሚፈታው ወጣቶች በባለቤትነት እንደ አባት እና እናት አርበኞች በአብሮነትና በብሔራዊ አርበኝነት መንፈስ ተላብሰው ለሰላም ሲታገሉ ነው ብለዋል ቢሮ ኃላፊው።

በሀገር አቀፍም ይሁን በክልል ደረጃ ከ70 በመቶ በላይ የሚኾነውን ወጣት ያላሳተፈ ምጣኔ ሃብታዊ ፣ ማኀበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ግቡን ሊመታ አይችልም ነው ያሉት አቶ እርዚቅ።

አሁን ላይ ክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት ምክንያት ከሰብዓዊ ጉዳት በተጨማሪ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በመስተጓጎላቸው መጠቀም ያለበት የኀብረተሰብ ክፍል እንዳይጠቀም አድርጎታል። ስለኾነም ይህን የሰላም እጦት ወደ ተሻለ ኹኔታ ማምጣት የሚቻለው ወጣቶችን አሳታፊ በማድረግ ነው። እናም የዓድዋን ድል ከሰላም ኮንፈረንሱ ጋር አስተሳስሮ ማካሄድ ተሞክሮ ለመውሰድ በእጅጉ ይጠቅማል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው።

ክልሉ የገጠመውን የሰላም እጦት የዛሬው ወጣት ወደ ምክክር እና ውይይት አምጥቶ ቁርሾው በሰላም የሚፈታበትን መንገድ ማመቻቸት ከወጣቱ ትውልድ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።

በኮንፈረንሱ በጠቅላላው ከ4ሺህ 168 ቀበሌዎች የተውጣጡ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ተሳታፊ ይኾናሉ ተብሏል። ለወጣቶቹም በክልላዊ እና በሀገራዊ ማንነት እንዲሁም በብሔራዊ ጥቅሞች የተሻለ ግንዛቤ ይፈጠርላቸዋል ነው ያሉት ኀላፊው። በጉባኤው በየዘመናቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበሩ ታዋቂ ግለሰቦችም ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ጣት ከመቀሳሰር ወጥተን ችግሮቻችን በውይይት መፍታት ያስፈልገናል” አባተ ጌታሁን (ዶ.ር)
Next article“እኛ የአገው ሕዝብ ሰላምን ከማንም የማንጠብቅ ሰላማችን በጃችን ያለ በመኾኑ ሰላማችንን የሚያውክ ሁሉ ልክ ወራሪው ጣሊያንን እንደታገልነው ሁሉ የምንታገለው ይኾናል” አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ