”ጣት ከመቀሳሰር ወጥተን ችግሮቻችን በውይይት መፍታት ያስፈልገናል” አባተ ጌታሁን (ዶ.ር)

14

ባሕር ዳር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከአዲስ ህይወት ሪሃብሊቴሽን ኤንድ ሪኢንተግሬሽን አሶሴሽን (አህራ) ጋር በመተባበር የአማራ ክልል የሰላም ፎረም ተቋቁሟል።

በማቋቋሚያ ሥነ ሥርዓቱ በሰላም መሠረታዊ ምንነት እና አስፈላጊነት እንዲሁም የሰላም መደፍረስ እያስከተለ ስላለው ሁለንተናዊ ቀውስ ላይ ውይይት ተደርጓል።ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በተለይም የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም ጠንቅ የኾኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መሥራት እንዳለባቸው ተመላክቷል። ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላም ለመፍትሔያቸው በመሥራት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ተብሏል።

ፎረሙ ለክልሉ ሰላምና ልማት በጎ ሚና የሚጫዎት፣ ልዩነቶችን በመግባባት የሚፈታ፣ ሁከትን የሚጠየፍ፣ በውይይት ባህል የሚያምን ማኅበረሰብ የመፍጠር፤ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሚያስችል አደረጃጀትና አሠራር የመገንባት ዓላማ ያለው እነረደኾነም ተገልጿል።

በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) መንግሥት እና የጸጥታ አካሉ ብቻ ሰላም ሊያረጋግጥ አይችልም ብለዋል።

የጦርነትን አውዳሚነት የገለጹት አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) በ2013/14 ዓ.ም በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት በሀገር ደረጃ በቁሳዊ ብቻ 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ነው የጠቀሱት። አሁንም በአማራ ክልል ያለው ግጭት የከፋ ውድመት እያስከተለ መኾኑን አመላክተዋል።

ጣት ከመቀሳሰር ወጥቶ ችግሮችን በመወያየት መፍታት እንደሚያስፈልግም’ ገልጸዋል። ስህተታችን ራሳችን እያረምን መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ በክልሉ ላጋጠመው የሰላም ችግር መፍትሔ ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ለማስቻል የፎረሙን አስፈላነት ገልጸዋል። ”በሰላም እጦቱ ተጎጂው ማኅበረሰቡ ስለኾነ ለሰላሙ መሥራት አለበት” ብለዋል።

የተቋቋመው የሰላም ፎረሙ ካካተታቸው የመንግሥት እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር መሥራት ሰላምን ለማስፈን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።የአማራ ክልል ሲቪል ሶሳይቲ ጥምረት ሥራ አስኪያጅ ንጋቱ ደስታ የሰላም ፎረም መቋቋሙ አማራ ክልል ላለበት የሰላም እጦት ችግር አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል። ፎረሙ ውጤታማ እንዲኾን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አካታች መኾን እንዳለበት ጠቁመዋል። በፎረሙ የአንድ ወገን ሃሳብ ብቻ ሳይኾን የሁሉም ሃሳብ ሊደመጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ስለኾነም 29 የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የፎረሙ አባል ኾነው ተዋቅረዋል። ሥራ ሲጀመር በሂደት መሻሻል እና መዳበር ያለባቸው ጉዳዮች እንደሚኖሩም ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአገው ሕዝብ ለልማት፣ ለፍትሕ እና ለዴሞክራሲ ተምሳሌት ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን”
Next article“የሰላም እጦቱ ችግር የሚፈታው ወጣቶች በብሔራዊ አርበኝነት መንፈስን ተላብሰው ለሰላም ሲታገሉ ነው” የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ