“የአገው ሕዝብ ለልማት፣ ለፍትሕ እና ለዴሞክራሲ ተምሳሌት ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን”

15

ባሕር ዳር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 84ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ በዓል በእንጅባራ ከተማ እየተካሄደ ነው። በበዓሉ ላይ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን እና ሌሎችም የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን “ፈረሰኝነት የአርበኝነች እና የጀግንነት ምልክት ከኾነ፤ አርበኝነት እና ጀግንነት ደግሞ ለብሔራዊ እና ለወንድማማችነት ማሰሪያ ቁልፍ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አርበኝነት ለሀገር፣ ለሕዝብ እና ለፍትሕ መታመን ነው፤ የአገው ፈረሰኞችም ሀገር በተወረረች ወቅት ፈረሳቸውን ይዘው በመዝመት የሀገርን እውነተኛ ፍቅር አሳይተዋል ብለዋል።

የአገው ፈረሰኞች ማኅበር እስካሁን ድረስ ጸንቶ መኖሩ እና ማደጉ ሕዝቡ ለሀገር ክብር እና ለፍትሕ ያለውን ቀናኢነት የሚያሳይ ስለመኾኑም ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል። ሕዝቡ ዛሬም ባለንበት አውድ ውስጥ ለሰላሙ ዘብ የሚቆም እና ለሀገር እና ለሕዝብ ታማኝ መኾንን በተግባር እያሳየ ነው ብለዋል።

አርበኝነት ቁጭ ብሎ መነጋገርን፣ ነገሮችን በእኩልነት መመልከትን እና አንዱ በሌላው ጫማ ውስጥ ኾኖ ማሰብን ይጠይቃል፤ አሁን ያለንበት አውድም ችግሮችን በውይይት እና በንግግር በመፍታት ሀገር የማጽናት ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ እንደኾነ አስገንዝበዋል። ሕዝብ እና መንግሥት በእውነተኝነት እና በሀቀኝነት ላይ ተመሥርተው ችግሮችን መፍታት ይገባልም ብለዋል። ይህንን ሥልጡን አካሄድ ወደኃላ በመግፋት ችግሮችን በነፍጥ ለመፍታት መሞከር ግን መፍትሔ የማያስገኝ ተላላነት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የራሳችንን ቤት አቃጥለን የምንሞቅ ተላላ ሕዝቦች መኾን የለብንም፤ ይልቁንም በመከባበር እና በመደማመጥ ችግርን እየፈታን ሀገር መገንባትን መለማመድ አለብን ሲሉም ተናግረዋል። በመኾኑም ነፍጥ አንስተው ችግርን ለመፍታት የሚያስቡ ወገኖች በሙሉ አካሄዳቸው በራሳቸው፣ በሕዝብ እና በክልሉ ላይ የሚያመጣውን መዘዝ በውል በመረዳት ከድርጊታቸው መታረም አለባቸው ብለዋል። ይሕ እንዲኾን ደግሞ መንግሥት የዘረጋውን የሰላም ጥሪ መቀበል እና ሰላምን መምረጥ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።

የነፍጥ አካሄድ በሚወልደው ችግር የሚጎዱትን ወገኖች፣ የሚደቅቀውን ኢኮኖሚ፣ የሚደርሰውን ችግር ለመቅረፍ ነፍጥን አስቀምጦ ለንግግር እና ለውይይት ዝግጁ መኾን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ “የአገው ሕዝብ ለልማት፣ ለፍትሕ እና ለዴሞክራሲ ተምሳሌት ነው” ሲሉም ገልጸዋል። ሰላም የሚጸናውም ከንግግር ባለፈ ልማት፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲን በማጽናት ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የኾነ ሕዝባዊ ማኅበር ነው” አለቃ ጥላየ አየነው
Next article”ጣት ከመቀሳሰር ወጥተን ችግሮቻችን በውይይት መፍታት ያስፈልገናል” አባተ ጌታሁን (ዶ.ር)