
ባሕር ዳር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላማዊ አርበኝነት ለወንድማማችነት” በሚል መሪ ሃሳብ 84ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ ክብረ በዓል በእንጅባራ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡
በ1932 ዓ.ም የተመሠረተው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር አሁን ላይ 62 ሺህ 221 አባላት አሉት ያሉት የአገው ፈረሰኞች ማኅበር አለቃ ጥላየ አየነው ማኅበሩ በእድሜ አንጋፋ እና በአደረጃጀት የበረታ ማኅበር ነው ብለዋል፡፡ የማኅበሩ አባል ለመኾንም 18 ዓመት መሙላት ብቻ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በየደረጃው ከስድስት ሺህ በላይ ሥራ አስፈጻሚዎች አሉት ያሉት አለቃ ጥላየ አየነው የተጣላን በማስታረቅ፣ የተቀማን በማስመለስ፣ የተበደለን በማስካስ፣ የታመመን በመጠይቅ እና የሞተን በመቅበር ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ ማኅበር እንደኾነ አንስተዋል፡፡
“የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የኾነ ሕዝባዊ ማኅበር ነው” ያሉት አለቃ ጥላየ አየነው ማኅበሩን ለየትኛውም የፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም የሚሞክሩ ሁሉ ማኅበሩን የማይወክሉ ናቸው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!