
ጎንደር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ የሰላም አስከባሪ አባላት የተሃድሶ ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል። የጠገዴ ወረዳ ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤተ ኀላፊ ላቀው አዛናው የተሃድሶ ሥልጠናው በወረዳው በሚገኙ 22 ቀበሌዎች የተወጣጡ አባላትን ያሳተፈ መኾኑን ገልጸዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ በአመለካከት፣ አስተሳሰብ እና በሥነ ልቦና ዝግጁ ኾኖ በወረዳው ያለውን ሰላም የሚያጸና እንዲኾን የተሃድሶ ሥልጠናው እየተሰጠ ነው ብለዋል።የጠገዴ ወረዳ ሰላሙን እስካሁን ጠብቆ ያቆየ በመኾኑ ሥልጠናው በአካባቢው የሚታዩ ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል አጋዥ ነው ይላሉ።
ሥልጠናውን የሚወስዱ የወረዳው ሰላም አስከባሪ አካላት አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለመመለስ ቁርጠኛ ስለመኾናቸው ለአሚኮ ተናግረዋል።የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጎሸ አምባሁን ሥልጠናው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሚገኙ 15 ወረዳዎች 4 ከተማ አሥተዳደሮች የሚሰጥ መኾኑን ገልጸዋል።
የአካባቢው የሰላም አስከባሪዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና የሚያገኙ በመኾኑ ለአካባቢያቸው ሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ ይረዳል ብለዋል። የሰላም ማስከበር ሥራው ማኅበረሰብን ያሳተፈ ነው ያሉት ኀላፊው አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለማምጣትም የጸጥታ መዋቅሩ ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ ይሠራል ነው ያሉት።ሥልጠናው ለ10 ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ መኾኑም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ዳንኤል ወርቄ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!