
ባሕር ዳር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት የሥነ-ምግባር ጥሰት ፈጽመዋል በተባሉ አመራር እና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታውቋል።
አገልግሎቱ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ የተጠያቂነት ሥርዓትን ለማስፈን ባከናወነው ሥራ እርምጃው መወሰዱን ነው የገለጸው። ተቋሙ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ከደንበኞች ከቀረቡለት 63 ጥቆማዎች ውስጥ የማጣርት ሥራ በማከናወን፤ በ23 አመራር እና ሠራተኞች ላይ ላይ ከጹሑፍ ማስጠንቂያ እስከ ስንብት የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታውቋል።
በተጨማሪም በተቋሙ በውስጥ የሥነ ምግባር ችግር በታየባቸው 409 ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አሥተዳደራዊ እርምጃዎች እንደወሰደም ገልጿል። በዚህም በ106 ሠራተኞች ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣በ282 ሠራተኞች ላይ የደመወዝ ቅጣት፣ በ11 ሠራተኞች ላይ ስንብት እንዲሁም በ10 ሠራተኞች ላይ ባደረገው ማጣራት ነጻ እንዳላቸው ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ተቋሙ ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች እና ጥቆማዎችን ለመቀበል ከተዘረጉ የ905 እና 904 ነጻ የጥሪ ማዕከላት በተጨማሪ፤ ደንበኞች ቅሬታቸውን ቀላልና ምቹ በኾነ መንገድ ማቅረብ የሚችሉበት ዘመናዊ የሙስና ጥቆማ መቀበያ ሥርዓት ለመዘርጋት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁሟል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!