“ኅብረት የቁጥር መብዛት ብቻ ሳይኾን የልብ አንድነትም ያስፈልገዋል” የደብረ ብርሀን ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ መንግሥቱ ቤተ።

20

ደብረ ብርሃን፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሀን ከተማ ምክርቤት 4 ኛ ዙር 11ኛ ዓመት 40ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል። በጉባኤው ላይ ባለፉት 6 ወራት የተከናወኑ ዓበይት ተግባራት ከአስፈጻሚው አካል ጋር ይገመገማሉ።

የጉባኤውን መክፈቻ ንግግር ያቀረቡት አፈ ጉባኤው መንግሥቱ ቤተ ለሕዝብ እና ለሀገር የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለማከናወን የአገልጋይነት መንፈስ እና ስሜትን የተላበሰ ባለሙያ እና አመራር መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

“ምክር ቤቶች የሕዝብ ሉዓላዊነት መገለጫ ናቸው” ያሉት አቶ መንግሥቱ የሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት እና በአገልግሎት ለማርካት አመራሮች እና ባለሙያዎች ቁርጠኛ ሊኾኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሰላም ለልማት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የጠቆሙት አፈ ጉባኤው የደብረ ብርሃን እና የአካባቢው ነዋሪዎች ሰላማቸውን ለማስጠበቅ ከመቸውም ጊዜ በላይ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል። አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ ደግሞ በጋራ መቆም እና በኅብረት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። “ኅብረት የቁጥር መብዛት ብቻ ሳይኾን የልብ አንድነት ያስፈልገዋል” ሲሉም ተናግረዋል።

የደብረ ብርሀን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ደብረ ብርሀን ከተማን የኢንደስትሪ፣ የቴክኖሎጂ፣ የቱሪዝም እና የግብርና ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። የታዩ መልካም አፈጻጸሞች እና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮችም በምክር ቤቱ ውይይት ላይ ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ:- ዮናስ ታደሰ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ያካሂዳል።
Next article“የሥነ ምግባር ችግር በታየባቸው 409 ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አሥተዳደራዊ እርምጃዎች ወስደናል” የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት