
ባሕር ዳር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር ክብር በኾነው የሰንደቅ ዓላማ ቀለም የተሸለሙ ፈረሶች እና በላያቸው ላይ በክብር ተቀምጠው የሚኮለኩሏቸው ፈረሰኞች የአገው ሕዝብ ልዩ ድምቀቶች ናቸው።
በአገው ምድር በየትኛውም ዓይነት የአደባባይ ማኅበራዊ ክዋኔዎች ፈረሰኞች እና ፈረሶቻቸው ደምቀው ይስቸዋላሉ። ፈረሶች እና ፈረሰኞች በደስታውም በሃዘኑም ተካፋይ ናቸው። በሰርግ፣ በለቅሶ፣ በንግሥ እና በእንግዳ አቀባበል የፈረሶች ሰልፍ አይጠፉም።
ምጣኔ ሃብቱን በመደገፍ ረገድም ከእርሻ እስከ መጓጓዣ የፈረሶች ሚናቸው የላቀ ነው። ፈረስ ለአገው ሕዝብ ብዙ ነገሩ ነው። የሀገርን ሰንደቅ ከፍ በማድረግ በየሁነቱ የተለያዩ የአደባባይ ትዕይንቶች ያሳዩበታል። ይኸውም የአንድ ሰሞን የክብረ በዓል ትዕይንት ብቻ ሳይሆን ዘወትር በአኗኗራቸው የሚተገብሩት ነው። በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰንደቅ ዓላማ ያለውን ክብር ላስተዋለ ለሀገር የተከፈለውን መስዋዕትነት ማሳያ ምልክት ነው።
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በቀበሌ፣ በቀጣና፣ በወረዳ እና በዞን ደረጃ የተደራጁ አባላት እና የፈረስ አለቃዎች የተባሉ አመራሮች አሉት። ይህ መዋቅር በሁሉም የብሔረሰቡ ወረዳዎች የተዘረጋ ነው። በአሁኑ ወቅትም ከ62 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲኾን ከጊዜ ወደ ጊዜ አሠራሩን ለማዘመን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
የፈረሰኞቹ ሥራ አስፈጻሚዎች አመራረጥ በየአራት ዓመቱ የሚከናወን ሲኾን በዞን ደረጃ የፈረሰኞች ማኅበር ሥነ ሥርዓት በየዓመቱ ጥር 23 ነው የሚከበረው። የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በ2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ሀገራዊ ቅርስ ኾኖ ተመዝግቦ ዕውቅና ማግኘቱ ይታወቃል። በተጨማሪም ይህ ክብረ በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!