
ባሕር ዳር: ጥር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓልን ምክንያት በማድረግ ወደ ከተማዋ መጥተው የኢንቨስትመንት ቦታ ለሚጠይቁ ባለሃብቶች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቱን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ባለሃብቶች ደብረ ታቦርን በማልማት ራሳቸውን እና የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንዲያደርጉም ከንቲባ ደሴ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል።
በከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚመጡ ባለሃብቶች ለሥራ የተመቸ ሰላም መፈጠሩንም አስታውቀዋል። ከንቲባው ደብረ ታቦር ለኢንቨስትመንት የተመቹ የተለያዩ አማራጮች እንዳሏትም ተናግረዋል። ወደ ከተማዋ መጥተው ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ቦታ ለመስጠት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የከተማዋ ታሪክ ጠገብነት እና አሁን ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አይመጣጠንም ያሉት ከንቲባው ታሪኳን የሚመጥን የኢንቨስትመንት ሥራ መሥራት ግድ እንደሚል ገልጸዋል።
የጋፋት ኢንዱስተሪ ባላቤት የነበረችው ከተማ ቀድማ በጀመረችው ልክ አሁን ላይ በቂ ልማቶች እንደሌሏትም አስታውቀዋል። ደብረ ታቦርን በኢንቨስትመንት ወደፊት ያራምዳሉ ተብለው የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በሰላም ምክንያት ተስተጓጉለው መቆየታቸውንም አንስተዋል።
ስለ ደብረ ታቦር ታሪክ ከማውራት በዘለለ ተግባራዊ የኾነ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ እና ለዚህም ከተማ አሥተዳደሩ የበኩሉን ዝግጅት ማድረጉን ከንቲባው ገልጸዋል። በከተማዋ የነበረውን የኃይል አቅርቦት ችግር የሚፈታ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በከተማዋ የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው እየሠሩ ያሉ ባለሃብቶችን ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
በከተማዋ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት የተሻለ እንዲኾን ባለኮከብ ሆቴል ለሚገነቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ቦታ መሥጠታቸውንም አስታውቀዋል። ቦታ ወስደው በማያለሙ ባለሃብቶች ላይ የወሰዱትን ቦታ እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስዱም አመላክተዋል።
የጸጥታ መደፍረስ ባለሃብቶች በሚፈለገው ልክ እንዳያለሙ እንቅፋት እንደሚኾን የተናገሩት ከንቲባው የከተማዋ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
ደብረ ታቦር ታሪኳን የሚመጥን ኢንዱስትሪ እንዲኖራት ለማድረግ ሰላምን ማፅናት ቀዳሚው ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል። ወጣቶች ወደ ከተማዋ ለኢንቨስትመንት የሚመጡ ባለሃብቶችን በፍቅር እና በክብር እንዲቀበሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!