“የመርቆሬዎስን በዓል በደመቀ ኹኔታ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቀናል” የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር

39

ባሕር ዳር: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደብረ ታቦር ከተማ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል። በታሪካዊው የአጅባር ሜዳ የሚከበረው በዓለ መርቆሬዎስ የበርካታ እንግዶችን ቀልብ ይስባል።

ደብረ ታቦርም በዓሉን በድምቀት ስታከብረው ኖራለች። የዘንድሮውንም በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጨረሱን ከተማ አሥተዳደሩ አስታውቋል። የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን የቅዱስ መርቆሬዎስ ክብረ በዓል ጥር 25 በደብረ ታቦር በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል። በዓሉ ረጅም ታሪክ ያለው፣ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶች የሚታዩበት መሆኑንም ገልጸዋል።

“በዓሉን በደመቀ እና በአማረ ሁኔታ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቀናል” ነው ያሉት። ደብረ ታቦር እንግዶቿን ለመቀበል እየጠበቀች መኾኗንም ተናግረዋል።

ከተማዋ ከከተራ በዓል ጀምሮ በርካታ በዓላትን ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶችን በጠበቀ መልኩ በሰላም ስታከብር መቆየቷንም ገልጸዋል። በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ የጸጥታ ኃይሉ እና የከተማዋ ነዋሪዎች ቅንጅት የሚደነቅ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባው የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓልም ከእስካሁኑ በተሻለ መልኩ በድምቀት ይከበራል ነው ያሉት።

በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ ሰፊ ሥራዎችን መሥራታቸውን ነው የተናገሩት። እንግዳ ተቀባዩ የደብረ ታቦር ሕዝብም እንግዶችን ለመቀበል ዝግጁ መኾኑን ከንቲባው አረጋግጠዋል።

የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እና ሌሎች የምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያነቃቃም ተናግረዋል። አሁን ያለው የሰላም ኹኔታ በጸጥታ ችግር ቆመው የነበሩ የልማት ሥራዎችን ለማንቀሳቀስ እድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

በደብረ ታቦር ከተማ የሚከበሩ በርካታ በዓላትን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች በርካታ ታሪካዊ እና ሃይማኖት ሥፍራዎችን የማየት እድል እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለእንግዶች ለማሳየት ዝግጅት ማድረጉንም አስታውቀዋል። ወጣቶች በዓሉ በድምቀት እንዲከበር የሚያደርጉት ተሳትፎ የሚደነቅ መኾኑን ያነሱት ከንቲባው ዘንድሮም ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። በዓለ መርቆሬዎስን ለማክበር የሚመጡ እንግዶች የጸጥታ ስጋት እንደማይገጥማቸውም አስታውቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራውን በአንጎለላና ጠራ ወረዳ አስጀመረ።
Next articleበከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ባለሃብቶችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።