የተገኘውን ሰላም ማጽናት እና ማስቀጠል እንደሚገባ የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ተናገሩ።

25

ደቤ: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር ጸጥታ መምሪያ የተዘጋጀ ግምገማዊ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በከተማው ለሚገኙ የጸጥታ መሪዎች እና አባላት እየተሰጠ ይገኛል።

በከተማዋ ባለፉት ስድስት ወራት የተሠሩ የጸጥታ ሥራዎች በመድረኩ ተገምግመዋል፤ የቀጣይ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በደሴ ከተማ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ማሳደግ እና ማጽናት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአቅም ግንባታ ሥልጠናው ለተከታታይ 10 ቀናት ይቀጥላል ተብሏል። በከተማዋ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በማስቀጠል ሂደት ትኩረት እንደሚደረግ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በከተማዋ የተሠሩ የጸጥታ ሥራዎችን በመገምገም ለጸጥታ መሪዎች እና አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠናም እንደሚሰጥም አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ የደሴ ከተማን ሰላም ከሕዝብ ጋር በመኾን ለማስጠበቅ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። ደሴ አንፃራዊ ሰላም ልታገኝ የቻለችው ሕዝቡ እና አመራሩ ተቀናጅተው በመሥራታቸው መኾኑንም ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ ሕዝበ እና አመራር ተናበው በመሥራታቸው ከተማዋ በአንጻራዊነት ሰላማዊ ኾና መቆየቷ በመልካም ተሞክሮነት እንደሚጠቀስ የሥልጠናው ተሳታፊዎች ተናግረዋል። የተገኘውን ሰላም በማጽናት እና በማስቀጠል በኩል አስፈላጊውን ሁሉ ሥራ ከሕዝብ ጋር ለማከናወን ቁርጠኛ ስለመኾናቸውም ሠልጣኞች አረጋግጠዋል።

ለጸጥታ መሪዎች እና አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠቱ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ሠልጣኞቹ አንስተዋል።

ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዳግም ያገኙትን እድል ተጠቅመው የክልሉን ሕዝብ እና ሀገራቸውን ለመጠበቅ መዘጋጀታቸውን የተሃድሶ ሰልጣኞች ተናገሩ።
Next articleየአካባቢውን ሰላም የሚያረጋገጥ ብቁ የጸጥታ መዋቅር ለመገንባት እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።