
ባሕርዳር: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል መንግሥት የጠራውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ተሀድሶ ሥልጠና ለገቡ ሠልጣኞች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ተደረገላቸው ።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች አሥተባባሪ እና የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው፣ ሌተናል ጀኔራል መሀመድ ተሰማ የምስራቅ ዕዝ አዛዥ፣ ሌተናል ጀኔራል ብርሀኑ በቀለ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ እንዲሁም ኮሚሽነር ደስየ ደጀን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተገኝተዋል።
ውግንናችሁ ለሕገ-መንግሥቱ፣ ለሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እና ለሕዝብ መኾኑን አምናችሁ እና ተቀብላችሁ ስለመጣችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ደሳለኝ ጣሰው ናቸው።
ሌተናል ጀኔራል ብርሀኑ በቀለ በበኩላቸው ሀገር እና ሕዝብን ለመካስ ዳግመኛ እድል አግኝታችኋልና ይሄን እድል በአግባቡ በመጠቀም ሕገ ወጦችን በጽናት በመታገል እና በመመከት ለሀገራችሁ ዘብ መቆም አለባችሁ ብለዋል።
የሰላም ጥሪውን መቀበል በሕይዎታችሁም አዲስ ምዕራፍ መክፈት ነው ያሉት ሌተናል ጀኔራል መሀመድ ተሰማ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጥሩ ኃይሎችን ለመታገል ዳግመኛ እድል አግኝታችኋልና በአግባቡ ልትጠቀሙበት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም የተሀድሶ ሠልጣኞች የክልሉን ሕዝብ እንዲሁም ሀገራቸውን ለመጠበቅ ቃላቸውን ማደሳቸውን አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!