
ደብረ ማርቆስ: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደብረ ማርቆስ ከተማ እና በዙሪያው ባሉ ወረዳዎች ለሚገኙ የጸጥታ አካላት 2ኛ ዙር ሥልጠና በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተሰጠ ነው።
በሥልጠናው ላይ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ኮሎኔል ሃብቱ ከበደ ማኅበረሰቡ የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖረው እና በዞኑ የተገኘው አንፃራዊ ሰላም እንዲቀጥል የጸጥታ አካላት ሥልጠናውን በተገቢው መከታተል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ሰላም ከምንም በላይ ዋጋ አለው ያሉት ኮሎኔል ሃብቱ የጸጥታ አካላት ተቀናጅተው መሥራት እና የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት ሊያረጋግጡ ይገባል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም በመኖሩ የኅብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት እየሠሩ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የጸጥታ አካላት ያሉባቸውን ክፍተቶች በማየት የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው መልእክት አስተላልፈዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ የፖለቲካ አመራሩ እና የጸጥታ አካላት ያሉባቸውን ክፍተቶች በሥልጠናው በመሙላት ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ማስቀጠል የጸጥታ መዋቅሩ ኀላፊነት እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎችም እየወሰዱ ያሉት ሥልጠና ያሉባቸውን ክፍተቶች እንደሚሞላላቸው ነው የተናገሩት፡፡ያገኙትን ሥልጠና በመጠቀምም የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስከበር ቁርጠኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ሥልጠናው በደብረ ማርቆስ ከተማ እና በዙሪያው ካሉ ወረዳዎች ለተውጣጡ የጸጥታ አካላት እየተሰጠ ሲኾን ለሰባት ቀናት እንደሚቀጥልም ለማወቅ ተችሏል።
ዘጋቢ፡- አማረ ሊቁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!